Saturday, June 21, 2025

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የዐቢይ አህመድን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንደ ስጋት የሚቆጥሩት ለምንድነው?

ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የዐቢይ አህመድን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንደ ስጋት የሚቆጥሩት ለምንድነው?

ሰኔ 4/2017 ዓ.ም – ዞብል ፖስት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ምክር ቤቱ ባሳለፍነው ሳምንት ባካሄደው የ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 34ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ፣ የዐቢይ አህመድን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ “ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር፣ በተለይም ከኤርትራ ጋር፣ ወደ ጦርነት ሊያስገባት ይችላል” የሚል ስጋት ያዘለ አስተያየት ሰጥተዋል።

ዶክተር ደሳለኝ “የዐቢይ አህመድ መንግሥት የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ከፍተኛ መቃቃር የሚያስገባ እና ሀገሪቷን ዘላቂ አጋር የሚያሳጣ ነው” በማለት ነበር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ ጠንካራ ትችት የሰነዘሩት።

ዶክተር ደሳለኝ ስጋታቸውን ሲገልፁ፣ “ዐቢይ አህመድ የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ወጥነት የጎደለው እና በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ስትራቴጂያዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች የሚፈልጉትን ከፍተኛ ጥንቃቄ ችላ የሚል ነው” ብለዋል።

ዶክተር ደሳለኝ በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ የዐቢይ አህመድ መንግስት ከኤርትራ ጋር ጀምሮት መልሶ ያቋረጠውን ሰላማዊ ግንኙነት እና ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል ተደርጎ መልሶ የፈረሰውን የወደብ የመግባቢያ ስምምነት ለአብነት ያህል በመጥቀስ፣ የስጋታቸውን ትክክለኛነት አሳይተዋል። አክለውም፣ “ከኤርትራ ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት አሁን ላይ ወደ ጦርነት እያመራ ይገኛል፤ ከሶማሌላንድ ጋር ተጀምሮ የነበረው ግንኙነትም ከሶማሊያ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ አስገብቶናል” ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ምላሽ

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በበኩላቸው፣ “መንግሥት ከኤርትራ ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ አይገባም” በማለት ለዶክተር ደሳለኝ ትችት መልስ ሰጥተዋል። ሚንስትሩ አያይዘውም፣ “ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጥቅሞቿን ስታነሳ ትኩሳታቸው የሚጨምርባቸው አገራት አሉ፤ ሆኖም ግን መንግሥት በስትራቴጂክ አገራዊ ጥቅሞች ላይ ያለው አቋም አይዛነፍም” በማለት የዶክተር ደሳለኝን ስጋት ውድቅ ለማድረግ ሞክረዋል።

በርግጥ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ይህንን ይበሉ እንጅ፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ግን ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ እንዳሉት ወጥነት እና ጥንቃቄ የጎደለው፣ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ጉዳዮች በስጋትነት የሚታይ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች ሊቀርቡ ይችላሉ።

ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የዐቢይ አህመድን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንደ ስጋት የቆጠሩት በምን ምክንያት ነው?

ከዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት፣ ዐቢይ አህመድ እና ሙሴ ቢሒ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ “ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት ሆነች” ተብሎ በአገዛዙ ሚዲያዎች በሰበር ዜና መነገሩ ይታወሳል።

ይሄንን የመግባቢያ ስምምነት ዐቢይ አህመድ የግል ስኬቱ አድርጎ፣ እንደ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ያሉ ቁልፍ መስሪያ ቤቶችን ከጉዳዩ ባገለለ መልኩ ስምምነቱን በግሉ እንዳስኬደ እና ይፋ እንዳደረገው ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ተቋማዊ እና በመርህ የሚመራ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንደሌላት በግልፅ የሚያሳይ አንድ ወሳኝ ክስተት ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

በፈረንጆቹ 2024 መግቢያ በአዲስ አበባ ከሶማሌላንድ ጋር ተደረገ የተባለው የወደብ ስምምነት በርካታ ቀጠናዊ ቀውሶችን አስከትሏል። በቅድሚያ ቱርክን የሶማሊያ የውሃ ጠረፍ ጠባቂ እና የተፈጥሮ ሀብት አልሚ ያደረገበት ሲሆን፣ ስምምነቱ የተቀደደበት በዐቢይ አህመድ እና በሶማሊያውያን ፕሬዚዳንት ሀሠን ሼኽ ሙሐሙድ የተፈረመው ሌላኛው “የአንካራ ዲክላሬሽን” ደግሞ የቱርኩን ጣይብ ኤርዶጋን ከአፍሪካ ቀንድ አድራጊ ፈጣሪ የውጭ ኃይሎች መካከል አንዱ እንዲሆን ያደረገበት ክስተት ነበር።

በዐቢይ እና ሶማሌላንድ መካከል የተደረገው ስምምነት፣ በአንድ በኩል በጦርነትና ውጥረት የሚታወቀውን የአፍሪካ ቀንድ ወደባሰ ውጥረት ያስገባ፤ አለፍ ሲልም በ2020 ተመስርቶ ከነበረው የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ እና ሶማሊያ የሶስትዮሽ የትብብር ማዕቀፍ፣ ኢትዮጵያን ሰርዞ ግብፅን የጋበዘበት ክስተት ሆኖ ማለፉን ተመልክተናል።

ከዚህም ባሻገር፣ ግብፅ እና ሶማሊያ አዲስ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥምረት እንዲፈጥሩ አስችሏል። ግብፅም ከአርባ አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ያደረገችበትንና ወታደሮቿንም በአፍሪካ ቀንድ ለማሰማራት የቻለችበትን ዕድል ፈጥሮላታል።

ዐቢይ አህመድ ከሶማሊያ ጋር የፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ቱርክ አንካራ ላይ ከተሰረዘ በኋላ፣ የወደብ ባለቤትነት ፍላጎቱን ወደ ኤርትራ ያዞረበት ሂደት ተፈጥሯል። በርግጥ ዐቢይ አህመድ የወደብ ጉዳይን አጀንዳ ማድረግ ከጀመረበት ከሁለት ዓመታት ወዲህ ጀምሮ፣ ገና ከሶማሌላንድ ጋር ስምምነት ሳይፈረም በፊት ነበር ኤርትራ የብልፅግናውን አገዛዝ በስጋትነት መመልከት የጀመረችው።

የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከህወሓት ጋር በፕሪቶሪያ የተፈራረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከሰባት ዓመታት በፊት ተፈጥሮ የነበረው ሰላማዊ ግንኙነት በይፋ መልሶ ሊሻክር ችሏል። 

ከዚህ ጊዜ ወዲህ፣ ኤርትራ ፊቷን ወደ ግብፅ ያዞረችበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተከታታይ ወደ ካይሮ ተጉዘው ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር መክረዋል። በሉዓላዊነት እና ድንበር ጉዳዮች ላይም የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። አልሲሲ እና የግብፅ የደህንነት ባለስልጣናትም እንዲሁ ወደ አስመራ ተመላልሰዋል።

ይህ በአፍሪካ ቀንድ ፈጣን ለውጥ ነበር። የዐቢይ እና ኢሳያስ ኩርፊያ ውስጥ መግባት እንዲሁም የብልፅግናው አገዛዝ የቀይ ባህር አጀንዳ፣ ኢትዮጵያን በጎረቤት ሀገራት እንደ ስጋት እንድትታይ አልፎም የኢትዮጵያን ታሪካዊ ተቀናቃኞች ደግሞ ወደ አፍሪካ ቀንድ ስቦ ያመጣ የቀጠናው ትኩሳት ሊሆን ችሏል። ከዚህ አንፃር ግብፅ ከኤርትራ እና ሶማሊያ በተጨማሪ፣ ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ከጅቡቲ ጋር ያደረገችው ስትራቴጅክ ስምምነት አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

እነዚህ ለውጦች፣ ኢትዮጵያን የውጥረት እና የስጋት ቀጠና በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ከሚገኙ ጎረቤቶቿ እንድትነጠል ያደረጉበትን ሁኔታ ፈጥሯል። ዛሬ ላይ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ እና ከጅቡቲ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባችበት ጊዜ ነው።

ሱዳንንም ብንመለከት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገቡት ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች፣ ኢትዮጵያ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ የሆነውን ጄኔራል ሀምዳን ዳጋሎን ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጋር ሆና እየደገፈች ነው። ግብፅ እና ኤርትራ ባንፃሩ፣ የብሔራዊ ጦር መሪ የሆነውን ጄኔራል አልቡርሃንን እየደገፉ ነው። ይህ ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ በሱዳን ጉዳይ ጭምር ከጎረቤት ሀገሮች በተቃራኒ መቆሟን ያሳያል።

እነዚህ እና መሰል ሁኔታዎች ናቸው እንግዲህ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የዐቢይ አህመድ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ጦርነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት እንዲያጭርባቸው ያደረጉት።

ተቋማዊ አሰራር የጎደለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ!

ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት የሚመለከቱ በርካታ ውሳኔዎችን ወስኗል። በዚህ ረገድ የመጀመሪያው የጠቅላይ ሚንስትሩ ውሳኔ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መቀየር ነበር። 

ውሳኔውን ተከትሎ በፈረንጆቹ 2002 ዓ.ም የፀደቀውን “The FDRE Foreign Affairs and National Security Policy and Strategy” የተሰኘውን የውጭ ግንኙነት እና ብሔራዊ ደህንነትን አጣምሮ የያዘውን ሰነድ፣ በ2011 ዓ.ም “የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ” በተሰኘ አዲስ ረቂቅ ሊቀየር ችሏል።

በርግጥ የቀድሞውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለማሻሻል የሚያስገድዱ በርካታ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ፣ እና ዓለምአቀፋዊ ክስተቶች ተፈጥረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰላማዊ ግንኙነት መጀመራቸው፣ በቀይ ባህር እና የኤደን ባህረሰላጤ አካባቢ የኃያላኑ እና የቀጠናው ተዋናዮች ሽኩቻ መበርታት፣ የደቡብ ሱዳን እንደ አዲስ ሀገር ሆኖ መፈጠር፣ በሶማሊያ የማዕከላዊ መንግሥቱ እየተጠናከረ መምጣቱ፣ እና መሰል መሰረታዊ ጉዳዮች ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን እንድታሻሽል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ነበሩ።

ይሄንን ሁኔታ ተከትሎ፣ ዐቢይ አህመድ እንዲረቀቅ ባደረጉት አዲሱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እና ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ለሚኖራት መልካም ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ በግልፅ ሰፍሯል።

አዲሱ የውጭ ግንኙነት ፖሊስ ረቂቅ፣ ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር፣ አዳዲስ የትብብር ማዕቀፎችን መፍጠር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በዓለም መድረኮች የምታራምዳቸው አቋሞች የጎረቤት ሀገሮችን ጥቅምና ፍላጎት ከግምት ባስገባ መልኩ ይሆናል የሚሉ ሃሳቦች ሰፍረውበታል።

ወደ ተግባራዊነቱ ሲገባ ግን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርህን እና ተቋማዊ አሰራርን የተከተለ ሳይሆን፣ ሁሉም ነገር በዐቢይ አህመድ ግላዊ ፍላጎት ላይ ብቻ እንዲሆን ተወስኗል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ በ2011 ዓ.ም ያደረጉትን የስምምነት ጭብጦች ጨምሮ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር የምታደርጋቸው ግንኙነቶች በሙሉ ለህዝብ ይፋ የማይደረጉ እና ተቋማዊ ሂደቶችን ያልተከተሉ ሆነዋል።

ሌላ ተጨማሪ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ በፈረንጆቹ 2024 ዓ.ም መግቢያ ላይ ዐቢይ አህመድ እና የቀድሞው የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሒ ያደረጉት “የወደብ የመግባቢያ ስምምነት” ሲፈረም፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር የነበሩት አቶ ደመቀ መኮንን ጉዳዩን ያወቁት እንደማንኛውም ዜጋ ስምምነቱ ሲፈረም እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች ወጥተው ነበር።

በእነዚህ እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊስ ተቋማዊነቱን አጥቶ፣ በዐቢይ አህመድ ግላዊ ፍላጎት ብቻ ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን ተደርጓል ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት መሻከር

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት መሻከር የጀመረው ዐቢይ አህመድ በፈረንጆቹ መጋቢት 2021 የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ በሚወጡበት ጉዳይ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በአስመራ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ መሆኑን ብዙዎች ያነሳሉ። 

በፌዴራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ ጊዜ አንስቶ ደግሞ፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ውጥረት እያየለመበት መጥቷል። ውጥረት የነገሰበትን የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ጉዳይ ለየት የሚያደርገው፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሁለቱ ሀገራት አንዳቸው የሌላኛውን ተቃዋሚ ኃይሎች የመደገፍ፣ የማደራጀት እና የማስታጠቅ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው ነው። 

የዐቢይ አህመድ መንግሥት የኢሳያስን መንግሥት ለመጣል እየተንቀሳቀሰ ያለውን ብርጌድ ንሓመዱ የተሰኘውን የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይል በቅድሚያ አዲስ አበባ ቢሮ እንዲከፍት፣ በመቀጠልም በኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና እንዲጀመር ማድረጉ ተሰምቷል።

የኤርትራ መንግሥት ባንፃሩ፣ በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ፣ በደብረብፅዮን ከሚመራው አንጃ ጋር ግንኙነት መፍጠሩ በመነገር ላይ ይገኛል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ “ፅምዶ” የተሰኘ የኤርትራን እና የደብረፅዮንን የህወሓት ቡድን የያዘ ጥምረት በቅርቡ ተፈጥሯል። በዚህ ጥምረት ውስጥ ከሁለቱ ኃይሎች የተውጣጡ ወታደራዊ እና የፖለቲካ መሪዎች፣ ዳያስፖራዎች፣ የሚዲያ ሰዎች ተካትተዋል።

ይህ ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የገቡበት ውጥረት ወደ ከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑን ያሳያል። ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ “ሁለቱ ሀገራት ወደ ጦርነት ሊያመሩ የሚችሉበት ዕድል አለ” የሚል ስጋት ያደረባቸው ከዚህ እና ተያያዥ ቀጠናዊ ለውጦች ጋር የሚገናኝ ነው ብሎ መገመት ይቻላል።

የመደምደሚያ ሀሳቦች

በመሆኑም፣ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የዐቢይ አህመድ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን እንደ ስጋት የቆጠሩበት ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ውስጥ እየታዩ ካሉ ፈጣን ለውጦች እና በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ ካለው ተጽእኖ ጋር በእጅጉ የተገናኘ ነው ማለት ይቻላል።

“በርግጥ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን ጦርነት በከፈተበት ሁኔታ እና ሀገሪቷ ካለችበት ውስጣዊ መዳከም አንፃር፣ ከጎረቤት ሀገር ጋር ወደ ጦርነት ለመግባት የሚያስችል አቅም አለ ወይ?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።

ይህ ጥያቄ ይዞት የሚመጣው ምላሽ ግን አስፈሪ ነው። ምክንያቱም ጦርነቱ የቀጠናው ሀገራት ጦርነት ብቻ አይሆንም። ልክ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በርካታ የውጭ ኃይሎች ተሳታፊ እንደሆኑበት ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራም ሆነ ከሌላ የጎረቤት ሀገር ጋር ወደ ጦርነት ብትገባ፣ ጦርነቱ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጀምሮ፣ የውጭ ኃያላን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉበት እና በፍጥነት እጃቸውን የሚያስገቡበት ቀጠናውን ለማያባራ ቀውስ የሚዳርግ ጦርነት የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች