ከአዲስአበባ ከተማ ሃምሳ ኪሎሜትር በማይሞላ ርቀት ላይ ከምትገኘው ጫንጮ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የውሃ ፋብሪካ፣ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ንፁሃን መታገታቸው ተሰምቷል።
ዛሬ ከከሰዓት ከጫንጮ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው ሰዮ የውሃ ፋብሪካ፣ በርካታ ሰራተኞች በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን ለዞብል ፖስት መረጃውን ያደረሱን የአይን ዕማኞች ገልፀዋል። ምንጮቹ አክለውም፣ “ቻይናውያን ሳይሆኑ አይቀሩም” ያሏቸው ሶስት የውጭ ዜጎች አብረው ታግተዋል።
እገታው የተፈፀመው በኦነግ ታጣቂዎች እንደሆነ መረጃውን ለመፅሔታችን ያደረሱት የአካባቢው ነዋሪዎች አክለው ገልፀዋል። ታጋቾቹ ወደየት እንደተወሰዱ እስካሁን ድረስ የታወቀ ነገር እንደሌለ ምንጮቹ አያይዘው ነግረውናል።
የኦነግ ታጣሚዎች በአዲስአበባ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎችን ጨምሮ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር ውጊያ ሲያደርጉ እንደሰነበቱ ይታወቃል።
የኦነግ ታጣቂዎች ከአዲስአበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ጫንጮ ከተማ ዙሪያ እገታውን የፈፀሙት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደምመላሽ ገብረሚካኤል “ሰዎች ወደፈለጉበት ቦታ መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሀገራዊ ሰላም ተፈጥሯል” ባሉ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው።
ኮሚሽነሩ ከቀናት በፊት በፋና ቴሌቪዥን ቀርበው፣ ዜጎች በነፃነት ወደፈልጉበት አካባቢ መንቀሳቀስ ይችላሉ የሚል መግለጫ የሰጡ ቢሆንም፣ የኦነግ ታጣቂዎች የኢትዮጵያ ዋና መቀመጫ ከሆነችው አዲስአበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኝ ስፍራ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ንፁሃንን ከሚሰሩበት ቦታ አግተው ወስደዋል።
ከሁነቱ እንደምንረዳው፣ የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት የሚናገሩት እና ነባራዊው የሀገሪቷ ሁኔታ ለየቅል መሆኑን ነው።