ሰኔ 13/2017 ዓ.ም—ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!
የጅቡቲ መንግሥት ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ “ሕገ-ወጥ ስደተኞች ናቸው” ያላቸውን በሀገሩ የሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ጠርንፎ የመመለስ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ የጅቡቲ መንግስት አስገዳጅ ትዕዛዝ ውስጥ ግን “ሰላማዊ መመለሻ ሀገር የለንም” ያሉ ኢትዮጵያውያን ሸሽተው ከተደበቁባቸው ቦታወች እየተለቀሙ አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ለሁቲ አማፂ ቡድን በታጣቂነት እየተመለመሉ እንደሆነ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ጅቡቲ በግዛቷ የሚኖሩ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያስቀመጠችው ቀነ-ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የሀገሪቷ ፖሊስ ኢትዮጵያውያንን ከያሉበት እያሰሱ በመያዝ እስር ቤት የማስገባት ዘመቻ ከፍቶ እንደነበር ባሳለፍነው የግንቦት ወር መገባደጃ መዘገባችን ይታወሳል።
ጅቡቲ ሕገ-ወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከግዛቷ እንዲወጡ ትዕዛዝ ካስተላለፈችና የተሰጠው የመጨረሻ ቀነ-ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን “ጋላፊ እና ደዋሌ” ተብለው በሚጠሩ የድንበር አካባቢዎች አቋርጠው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን “All East Africa” የተሰኘ ድረ-ገፅ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን እና የተራድኦ ድርጅት ሠራተኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቦ ነበር።
ይሁንና ዛሬም ድረስ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን በጅቡቲ የሚገኙ ሲሆን፣ ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑ በወጣትነት እድሜ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች “መረጋጋት ወደሌለባት ኢትዮጵያ ከምንመለስ ቀይ ባህርን አቋርጠን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንገባለን” በሚል በጅቡቲ የተለያዩ መጋዝኖች ውስጥ ተደብቀው እንደሚገኙ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ወደ ሀገራችን አንመለስም ያሉት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የጅቡቲ መንግሥት ወደ ሀገራቸው ጠርንፎ እንዳይልካቸው ለጅቡቲ የፀጥታ ኃይሎች ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እያስላኩ እንደሚከፍሉ መረጃውን ያደረሱን ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
በጅቡቲ ተደብቀው ከሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን መካከል፣ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለመሻገር ከሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ጋር እየተደራደሩ እና ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ለማስላክ እየተጠባበቁ ሲሆን፣ ይሄንን ማድረግ ያልቻሉ ደግሞ ከሁቲ አማፂያን ጋር ግንኙነት ባላቸው ደላሎች አማካኝነት ለታጣቂ ቡድኑ በግዳጅ ተላልፈው እየተሰጡ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ በየመን በስፋት የሚንቀሳቀሰው የሁቲ አማፂያን ከአልሸባብ እና በኤደን ባህረሰላጤ ከሚንቀሳቀሱ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ከጥቂት ወራት በፊት ተቀማጭነቱ በዱባይ የሆነው “Al Akhbar Al Aan” የበይነ መረብ ሚዲያ ያወጣው የምርመራ ዘገባ ያመላክታል።
የሁቲ ታጣቂዎች ከልሸባብ እና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ጋር የፈጠሩት ግንኙነት ቡድኑ በኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች እና የዓለምአቀፍ የወንጀል ቡድኖች ጋር በትብብር እንደሚሰራ የሚያመላክት ሲሆን፣ ሁኔታው በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለሁቲ አማፂያን በግዳጅ በታጣቂነት እየተመለመሉ ነው የሚለውን መረጃ የሚያጠናክር ሆኖ አግኝተነዋል።
በሌላ መልኩ፣ ቀይ ባህርን እና የኤደን ባህረሰላጤን በአደገኛ ጀልባዎች ለማቋረጥ ሲሞክሩ፣ በጀልባ መገልበጥ፣ በድንበር ጠባቂዎች ጥቃት፣ በረሃብ፣ በጥማት እንዲሁም በሰው አዘዋዋሪዎች ግፍ ሳቢያ ባለፉት አስር ዓመታት በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህይወታቸውን እንዳጡ የተባበሩት መንግሥታትን የፍልሰት ድርጅትን (IOM) ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘገባዎች ያሳያሉ።
ጅቡቲ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ህገ-ወጥ ናችሁ በሚል ባልተለመደ ሁኔታ ከግዛቷ ለማባረር የወሰነችው፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከጅቡቲ በተጨማሪ የወደብ እና የባህር በር አማራጮችን የማፈላለግ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት በተፈጠረው የጉርብትና መሻከር ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች ይገልፃሉ።
ጅቡቲ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን “ባልተለመደ ሁኔታ” ከሀገሯ እንዲወጡ መወሰኗ እና ይሄንን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ለሁቲ አማፂያን በግዳጅ በታጣቂነት መመልመላቸው፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራ በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን አስከፊ ውጤት ያመላክታል።