ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሚመኩባቸው እና በከፍተኛ ወጪ ካስገነቧቸው ፓርኮች፣ ሪዞርቶች፣ እና የመዝናኛ ስፍራዎች አንዱ የሆነው በዳውሮ ዞን የሚገኘው የሀላላ ኬላ ሪዞርት የሚያስገባው ገቢ፣ የሠራተኞቹን ወርሃዊ ደምወዝ መሸፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አንድ የሪዞርቱ ሠራተኛ ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሪዞርቱ ሠራተኛ፣ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሀላላ ኬላ ሪዞርትን የጎበኙት 8 የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እና 34 የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ብቻ እንደሆኑ በመግለፅ፣ ሪዞርቱ “የሰው ድርቅ መትቶታል” በማለት ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
የመረጃ ምንጫችን አክለውም፣ ሀላላ ኬላ ሪዞርት ስራ የጀመረ ሰሞን በተሰራለት ከፍተኛ የገፅታ ግንባታ ምክንያት፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ ያደረጉላቸው ዳያስፖራዎች፣ የመንግሥት ደጋፊ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ እና ጥቂት የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ሪዞርቱን በተከታታይ ጎብኝተውት እንደነበር በማስታወስ፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሀላላ ኬላ ተገልጋይ የሌለው ሪዞርት ሆኗል” በማለት የሪዞርቱን ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል።
በዚህም ምክንያት የሀላላ ኬላ ሪዞርት የሚያስገኘው ገቢ የሠራተኞቹን ወርሃዊ ደምወዝ መሸፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል። “ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ የሠራተኛ ቅነሳ ሊደረግ ይችላል የሚል ፍርሃት አድሮብናል” በማለት መረጃውን ያደረሱን የሪዞርቱ ሠራተኛ ስጋታቸውን አያይዘው ገልጸዋል።
ዐቢይ አህመድ ለፓርኮች፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ እና ሪዞርቶች ግንባታ ከ2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወይም ከ17 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። ይሁን እንጅ፣ እንደ ሀላላ ኬላ ያሉ ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰባቸው ሪዞርቶች በጎብኝዎች እጥረት ስራቸው አደጋ ላይ ወድቋል።
የሀላላ ኬላ ሪዞርት ከገጠመው ችግር ጋር ተያይዞ፣ የማያባራ ጦርነት፣ የመሰረተ-ልማት እጦት፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብዛት፣ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እና መሰል አንገብጋቢ ጉዳዮች ባጋጠሟት ሀገር፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት የሀገሪቷን ከፍተኛ ሀብት በቅንጡ ፕሮጀክቶች ላይ ማፍሰሱ፣ ለኢትዮጵያውያን የሚያስገኘው ፋይዳ እንደሌለ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።