Friday, June 20, 2025

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeማሕደረ-ታሪክፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ሲታወሱ!

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ሲታወሱ!

ሰኔ 12/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስማሕደረ-ታሪክ!

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ አልታዬ፣ የአዲስ አበባው ልጅ፣ ከተሜው አማራ፣ የሸዋው ባላባት፣ የአርበኞቹ ልጅ፣ ደሞም የምስራቅ ሰው፣ የድሬው ብላቴና፣ ከአባታቸው ከአቶ ወልደየስ አልታዬ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ፅጌ በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት በዛሬዋ ቀን በሰኔ 12/1920 ዓ.ም ነበር።

በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው ብላቴናው አሥራት ወልደየስ እናት እና አባቱ ገና በጨቅላነት ዕድሜው መፋታታቸውን ተከትሎ ከእናቱ ጋር ወደ ድሬዳዋ ማቅናቱን፣ ስለ ፕሮፌሰሩ የተፃፉ መዛግባት ያስረዳሉ። ሐረርጌው አሥራት፣ የምስራቁ ሰው አሥራት፣ የድሬው ልጅ አሥራት የልደት ቀን ዛሬ ነው።

አሥራት ወልደየስ ለብዙዎች ተምሳሌት የሆነውን ስብዕናቸውን ከገነቡላቸው የህይወት ምዕራፎች መካከል፣ በድሬዳዋ የቄስ ትምህርት ቤት ከየኔታ ለማ ወልደመስቀል ዘንድ መማራቸው አንዱ ነው። ድቁናንም በዚያው በድሬዳዋ ተቀበሉ። ፕሮፌሰር አሥራት ባለ ብሩህ አዕምሮ እንደሆኑ ማስመስከር የጀመሩትም በልጅነታቸው ከቀሰሙት የአብነት ትምህርት ጊዜ ጀምሮ ነው።  

ታዳጊው አሥራት የድቁናን ማዕረግ ከድሬዳዋ ካገኘ በኋላ ወደ ዘመናዊው የትምህርት ዓለም የተቀላቀለው በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ነበር። በዚህ ትምህርት ቤት የላቀ ውጤት በማምጣት ወደ ግብፅ ተጉዞ በእንግሊዞች ቪክቶሪያ ኮሌጅ ተማረ።

አሥራት ከግብፅ ቆይታ በኋላ፣ አሥራት ወልደየስ የሚለው ስም በኢትዮጵያም፣ በአፍሪካም፣ በመላው ዓለምም ዝነኛ እንዲሆን ወዳደረገው ወደ እውቁ የኤደንብራ ዩኒቨርስቲ አቅንቶ የህክምና ትምህርቱን ጀመረ። በ1946 ዓ.ም ደግሞ ትምህርታቸውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቀው ተመረቀ። ጂኒየሱ አሥራት ልደቱ ዛሬ ነው።

ዶክተር አሥራት ወልደየስ ከኤደንብራ ዩኒቨርስቲ በህክምና ከተመረቁ በኋላ ወደሚፈልጋቸው ህዝብ ወዲያውኑ ተመልሰው መጡ። በዘመኑ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሆኑ ተቋሙን ይመሩት በነበሩት ደጃዝማች ፀሐይ እንቁ ሥላሴ ተጠይቀው፣ ለጃንሆይም አማላጅ ተልኮ ነበር። ዶክተር አሥራት ግን ስልጣኑ ይቅርብኝ እኔ በሙያዬ ህዝቤን ማከምን እመርጣለሁ አሉ። ይህ ትሁቱ አሥራት የተወለደው በዛሬዋ ቀን ነው።

የሕክምና ሙያቸውንም ሀ ብለው ጀመሩ። ወደ ውጭ ሀገር ተልከው የተማሩ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የቀዶ ህክምና ባለሙያ፣ ሀብታሙንም፣ ደሃውንም፣ የንጉሳውያንን ቤተሰብም፣ ገበሬውንም፣ ወደ እሳቸው የሚመጣውን ሁሉንም በእኩል ዐይን እያዩ የሚያክሙት፣ የሚያድኑትም አሥራት ወልደየስ የተወለዱት በዛሬው ዕለት ነው።  

ተቋምን በማቆም እና በማፅናት የሚያምኑት ፕሮፌሰር አሥራት፣ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት፣ ስመጥሩን የጥቁር አንበሣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በያኔው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ስር በህክምና ኮሌጅነት እንዲቋቋም አድርገዋል። ጥቁር አንበሣ ሆስፒታልን የመሰረቱት፣ ያስተማሩበት፣ የመሩት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋገሩት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የልደት ቀን ዛሬ ነው።   

ሐኪሙ ፕሮፌሰር አሥራት ከዚህ ሁሉ የህይወት ጉዞ በኋላ ከሕክምና ሙያቸው ባሻገር እሳቸውን አጥብቆ የሚፈልግ የታሪክ እጥፋት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ይከሰት ጀመረ። የደርግ መንግሥት ወደቀ፣ ኢህአዴግ ስልጣን ያዘ፣ አማራ ያልተወከለበት የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ተባለ። ሕገመንግሥትም ፀደቀ።

ይህ ሁሉ ለውጥ በፍጥነት ሲከሰት ፕሮፌሰር አሥራት ራሳቸውን ጭንቅ ውስጥ አገኙት። ሐኪሙ ፖለቲካ ውስጥ ገቡ። ደርግ ከወደቀ ከአንድ ወር በኋላ በሰኔ 1983 ዓ.ም በተካሄደው ኮንፈረንስ ፕሮፌሰር አሥራት ተሳተፉ። በኮንፈረንሱ ኤርትራ ታዛቢ ነበረች። መገንጠሏ ደርግ ሊወድቅ አፋፍ ላይ እያለ ገና በበርሃ የተወሰነ ጉዳይ ነበር።

ፕሮፌሰር አሥራት በጉባኤው ላይ “ሀገር ለማስገንጠል ውክልና ተሰጥቶኝ አልመጣሁም” ሲሉ ተናገሩ። ሀገር የሰሩ፣ ያፀኑ፣ ስርዓተ-መንግሥት የገነቡ አባቶቻቸውን ስነልቦና በሰኔው ኮንፈረንስ ያንፀባረቁት ፕሮፌሰር አሥራት ልደት ዛሬ ነው።

በርግጥ የእሳቸው አቋም ቀድሞ የተወሰነውን የኤርትራን የመገንጠል እውነታ ባይቀይረውም፣ ፕሮፌሰር አሥራት ግን ታሪክ ተሻጋሪ፣ ከህሊና ተጠያቂነት፣ ከታሪክ ተወቃሽነት የነፁ ያደረጋቸውን ስራ ሰርተዋል። እንዲህ ያለው የአባቶቹ ልጅ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የተወለደው በዛሬው ቀን ነበር።

ከዚህ ጊዜ በኋላ የፕሮፌሰሩ የፖለቲካ ተሳትፎ እያደገ የመጣበት አስገዳጅ የታሪክ አጋጣሚ እየተፈጠረ ሄደ። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ፖለቲካዊ ውክልና ያልነበረው አማራ በመላ ሀገሪቱ መጠነ ሰፊ ጥቃት ይደርስበት ጀመረ። በደሙ ባፀናት ሀገር ላይ መገደል መፈናቀል መሳደድ በረታበት።

ይህ ሁኔታ አብዝቶ ረፍት የነሳቸው እና የአማራውን የመደራጀት አስገዳጅ ሁኔታ የተረዱት ፕሮፌሰር አሥራት ከሌሎች ንቁ ወገኖች ጋር በ1984 ዓ.ም መዐሕድን መሰረቱ። ሊቀመንበርም ሆኑ። አርቆ ተመልካቹ አሥራት። የሚመጣው አደጋ ቀድመው ያዩት አሥራት። የአማራው የቁርጥ ቀን ልጅ አሥራት የተወለዱት በዛሬው ቀን ነበር።

መዐሕድ በተመሰረተ በዓመቱ በደብረብርሃን ታሪካዊ እና ህዝባዊ የሆነ ታላቅ ስብሰባ ተደረገ። ፕሮፌሰር አሥራትም አማራ ጠል ኃይሎች ከየትኛውም ጊዜ በላይ ተጠናክረው በመጡበት በዛ ወቅት የአማራ ህዝብ ቀጣይ ዕጣፋንታ ከባድ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናገሩ። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠባት አሳሰቡ።

አማራው ከፋሽስት ጣሊያን የጀመረ የጥላቻ ትርክት ሲነዛበት የኖረ እና እንዲጠፋ የተፈረደበት ህዝብ መሆኑን አስረግጠው ተናገሩ። የአማራ ህዝብ በደርግ ስርዓት የደረሰበትን በደል እያስታወሱ፣ ሁኔታው በኢህአዴግ ዘመንም የከፋ እንደሚሆን እሳቸውን በጥሞና ለሚከታተለው የደብረብርሃን ስብሰባ ተሳታፊ ህዝብ አስገነዘቡ። እኚህ የአማራው ሰብሳቢ እና ጠበቃ አሥራት ናቸው በዛሬው ዕለት የተወለዱት።

ከደብረብርሃኑ ህዝባዊ ስብሰባ በኋላ የኢህአዴግ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ መደናገጥ ተፈጠረ። አማራ ጠሎች ውክልና የነፈጉት አማራ መሰባሰብ መጀመሩ ረፍት ነሳቸው። ይሄንን ፕሮፌሰር አሥራት የሚመሩትን ህዝባዊ ወኔ እና ቁጭት በአስቸኳይ እንቅጨውም አሉ።

በጊዜው የነበሩት ባለሥልጣናትም በመንግሥት ልሳኖች በኩል ፕሮፌሰር አሥራትን “ጦርነት ቀስቃሽ ነፍጠኛ” ብለው ከሰሷቸው። የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፈቱባቸው። አማራ ሲሰባሰብ ጠላቶቹ እንደሚርዱ፣ ሲደራጅ እንደሚድን፣ ለሀገሩም ዘብ እንደሚሆን ያሳዩት ፕሮፌሰር አሥራት የተወለዱት በዚህ ቀን ነበር።

ከዚህ ጊዜ በኋላ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ፕሮፌሰር አሥራትን በየሄዱበት ያዋክቧቸው ጀመር። ቀጥለውም በሀሰት ክስ ወንጅለው ወደ እስር ቤት ወረወሯቸው። ፕሮፌሰር አሥራት ከሐኪምነት ወደ ፖለቲካ ህይወት በገቡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ህይወታቸውን በእስር ቤት እንዲያሳልፉ ተደረጉ።ለአማራ ሲሉ ከክብራቸውና ታላቅ ስማቸው ወርደው፣ ለአማራ ህዝብ እንደ ሻማ ቀልጠው ውድ ዋጋ የከፈሉት አይተኬው ፕሮፌሰር አሥራት የተወለዱት በዛሬዋ ዕለት ነው።  

ፕሮፌሰር አሥራት የልብ ህመም ነበረባቸው እና በእስር ቤት እያሉ ህመማቸው እየበረታበቸው ሄደ። የኢህአዴግ መንግሥትም አጋጣሚውን የበቀል መወጣጫ ለማድረግ ህክምና ከለከላቸው። የጤንነታቸው ሁኔታ መባባሱ በመላው ዓለም ሲሰማ፣ እነ አመነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በበርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ብርቱ ውትወታ እና ልመና፣ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ከዚያም በውጭ ሀገር ህክምና እንዲያገኙ ተፈቅዶ ነበር።

ይሁንና ፕሮፌሰር አሥራት ህክምና ማግኘት በነበረባቸው ጊዜ መንግሥት ከልክሏቸው ነበርና የጤናቸው ሁኔታ በከፋ ሁኔታ ተባብሶ፣ ህክምና ሲያገኙ በነበረበት በአሜሪካን ሀገር ፔንሲልቬንያ ሆስፒታል በግንቦት ወር በ1991 ዓ.ም ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።

ለአማራ የታሰሩለት፣ በህመም የማቀቁለት፣ የተዋከቡለት፣ የአማራ መጠቃት ይቆም ዘንድ በድፍረት ከፊት ቀድመው በመገኘታቸው ሐኪም አጥተው የሞቱት ሐኪም አሥራት ወልደየስ የተወለዱት በዛሬው ቀን ነበር።  

ፕሮፌሰር አሥራት ሞታቸው መላውን ዓለም ያሳዘነና ትልቅ መነጋገሪያ የሆነ ክስተት ነበር። የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ህልፈት በእነ ኒው ዮርክ ታየምስ በእነ ዘ-ጋርዲያን ለመላው ዓለም ተዘግቧል። ፕሮፌሰሩ ዓለምአቀፍ ስብዕና ነበራቸውና።

ዞብል ፖስት የአዲስ አበባውን ልጅ፣ የሸዋውን ባላባት፣ የድሬዳዋውን ዲያቆን፣ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሰቃዩን፣ የቪክቶሪያ ኮሌጁን ወጣት ተማሪ፣ የኤደንብራውን የሕክምና ምሩቅ፣ ወገኖቹን በቅን ልብ አገልጋዩን፣ የጥቁር አንበሣ ሆስፒታል መስራቹን፣ የመዐሕድን መሪ፣ የአማራውን ጠበቃ፣ ሀገሩን ኢትዮጵያ ከልቡ የሚወደውን ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የልደት ቀን በማስመልከት ይሄንን ዘገባ በማጠናቀራችን ልባዊ ደስታ ይሰማናል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች