Saturday, June 14, 2025

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ሶማሊያ ውስጥ የትጥቅ ትግል ጀመረ።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ሶማሊያ ውስጥ የትጥቅ ትግል ጀመረ።

ግንቦት 30/2017 ዓ.ም-ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ! 

በአብዲራህማን ማህዲ የሚመራው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ክንፍ፣ መቀመጫውን በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ በማድረግ የትጥቅ ትግል መጀመሩን ዞብል ፖስት ከምንጮቹ ሰምቷል። በሶማሊያ የትጥቅ ትግል ጀምሯል የተባለው የኦብነግ ክንፍ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ድርጅቱ በቅርብ ለሁለት መከፈሉን ተከትሎ ነው።

ታጣቂ ቡድኑ ከስድስት ዓመታት በፊት ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ከኤርትራ ወደ ሀገር ቤት በመግባት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ የነበረ ቢሆንም፣ ኦብነግ ለሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ በአብዲራህማን የሚመራው ኃይል በሶማሊያ የትጥቅ ትግል መጀመሩን፣ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልፀዋል።

ለ33 ዓመታት ያህል በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀስ የነበረው ኦብነግ፤ ወደ ሰላማዊ ትግል ለመግባት የወሰነው ከዐቢይ አህመድ መንግሥት ጋር በነሐሴ 2010 ዓ.ም ስምምነት ላይ ከደረሰ በኋላ ነበር።

ይሁን እንጅ፣ በአብዲራህማን ማህዲ የሚመራው የኦብነግ ክንፍ፤ “ከመንግሥት ጋር ግንኙት አናደርግም፣ ቀጣይ የትግል ስልታችንን በተመለከተ ከሕዝብ ጋር ውይይት እናደርጋለን” ሲል ለቢቢሲ የአማርኛው የዜና ክፍል የገለፀው ባሳለፍነው የካቲት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

ታጣቂ ቡድኑ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን አቁሞ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ለአዲስ ትግል እያደራጀ እንደሆነ ያስታወቀው፣ በካቲት 23/2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነበር። ይሄንን ተከትሎ የኦብነግ ሌላኛው ክንፍ በሚያዚያ 1/2017 ዓ.ም ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ጉባኤ፣ አብዲራህማን ማህዲን ከሊቀመንበርነት አንስቶ በሌላ መተካቱ ይታወሳል። 

ውሳኔውን ተከትሎ የትጥቅ ትግል የጀመረው የኦብነግ ክንፍ በበኩሉ፣ በግንቦት 7/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የሶማሌ ክልል መንግስት በተቀናጀ መልኩ የፓርቲውን አመራር ለመበታተን እየሰሩ ነው” በማለት ምላሽ ሰጥቶ ነበር። ቡድኑ አክሎም፣ “የሶማሌ ክልል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በ2010 ዓ.ም የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ በመጣል ፓርቲውን ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገባ እያደረገ ነው” በማለት አስጠንቅቆ ነበር።

አብዲራህማን የሚመራውን ክንፍ ጨምሮ፣ ኦብነግ ከስድስት ዓመታት በፊት በኤርትራ አሥመራ ከተማ ከመንግሥት ጋር ያደረጋቸውን ተከታታይ ውይይቶቾን እና ስምምነቶቾን ተከትሎ፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጅ፣ “የዐቢይ አህመድ መንግሥት ቃሉን አጥፎ ያደረግናቸው ስምምነቶች እንዳይፈፀሙ አድርጓል” የሚል ቅሬታ በማቅረብ፣ በአብዲራህማን የሚመራው ክንፍ፣ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ሰላማዊ ትግል እያደረገ ካለው ኦብነግ በመገንጠል ወደ ትጥቅ ትግል መግባቱን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል። 

ወደ ትጥቅ የገባው የኦብነግ ክንፍ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ቃሉን አጥፎ እንዳይፈፀሙ አድርጓል ካላቸው ስምምነቶችመካከል፣ “የኦብነግ ታጣቂዎችን ወደ ክልሉ የፀጥታ ኃይል ማስገባት፣ በጦርነት የተጎዱትን መልሶ ማቋቋም፣ የኦጋዴንን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ መመለስ፣ በህዝቡ የተፈጠሩትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ቅሬታዎችንና መገለል በዘላቂነት መፍታት” የሚሉት ይገኙበታል።

ኦብነግ በ2010 ዓ.ም የሰላም ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት 18 ሺህ ገደማ ታጣቂዎች የነበሩት ሲሆን፣ ምን ያህሉ የቀድሞ ታጣቂዎቹ በአብዲራህማን ማህዲ የሚመራውን የኦብነግ የትጥቅ ትግል እንደተቀላቀሉ የታወቀ ነገር የለም።

ኦብነግ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ጀምሮበታል የተባለው የሶማሊያ አካባቢ፣ መካከለኛው ሸበሌ ቀጠና እንደሆነ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል። ቀጠናውን አልሸባብ በስፋት የሚንቀሳቀስበት እንደሆነ ከዚህ በፊት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። በያዝነው ዓመት መግቢያ ከአርባ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ያደረገችው ግብፅም፣ ወታደሮቿን ያሰፈረችው በዚሁ ኦብነግ የትጥቅ ትግል ጀምሮበታል በተባለው አካባቢ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ዐቢይ አህመድ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገውን የወደብ ስምምነት ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባችው ሶማሊያ፣ ለኦብነግ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ በግዛቷ ነፃ መሬት ያመቻቸች ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ተቀናቃኝ የሆነችው ግብፅ ደግሞ ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ፣ ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት እና የሎጅስቲክ ድጋፍ በማድረግ የአብዲራህማን ማህዲን ታጣቂ ቡድን ልታጠናክር ትችላለች ተብሎ ይገመታል።    

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች