የደርግን መውደቅ ተከትሎ፣ ኢህአዴግ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ግንቦት 1983 ዓመተ-ምህረት ወዲህ ባለው የስልጣን እና የክልሎች አወቃቀር ምክንያት፣ የአማራ ህዝብ የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎችን ከሚያነሳባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ራያ ነው። በዋናነት ራያ አላማጣ፣ አላማጣ ከተማ፣ ራያ ባላ፣ ራያ ኮረም፣ ራያ ኦፍላ፣ እና ራያ ዛታ የሚባሉ ስድስት ወረዳዎች፣ ከወሎ ክፍለ-ሀገር በጉልበት ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ተደርጓል በሚል ጠንካራ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች የሚነሱባቸው አካባቢዎች ናቸው።
እነዚህ አካባቢዎች ለ30 ዓመታት በትግራይ ክልል ስር ሲተዳደሩ ከቆዩ በኋላ፣ በጥቅምት 24፣ 2013 ዓመተ-ምህረት በፌዴራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተቀሰቀሰው የመጀመሪያ ዙር ጦርነት ማግስት፣ ከታህሣሥ 2013 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ በአማራ ክልል ስር መልሰው ሲተዳደሩ ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመጀመሪያ ትግራይን፣ በመቀጠልም የአማራ ክልልን ለቅቆ በወጣባቸው የ2013 ዓመተ-ምህረት የክረምት ወራት፣ አካባቢዎቹ መልሰው በህወሓት ቁጥጥር ስር ሊወድቁ ችለዋል።
እስከ ሸዋ ደርሶ የነበረው የህወሓት ሠራዊት በጦርነቱ የመጨረሻ ዙር ተሸንፎ ከአማራ ክልል ለቅቆ ከወጣ በኋላ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ያደርግ የነበረውን ግስጋሴ ራያ ቆቦ ላይ ገትቶ፣ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በህዳር 2015 ዓመተ-ምህረት ወደ ፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ሊገቡ ችለዋል።
የሠላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ፣ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳያቸው መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ በሚል፣ በፌደራል መንግሥቱ ስር ሆነው እንዲቆዩ ተወስኖ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ በራያ አዘቦ እና በራያ አላማጣ አዋሳኝ ድንበሮች እንዲሰፈር ተደርጎ ነበር።
ይሁንና ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ፣ የህወሓት ታጣቂዎች በሚያዚያ 2016 ዓመተ-ምህረት የወሰን እና የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በኃይል ተቆጣጥረው ሊይዙ ችለዋል። እነዚህ አካባቢዎች በህወሓት ታጣቂዎች ስር ከወደቁ አንድ ዓመት ያለፋቸው ሲሆን፣ በአካባቢው ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማህበራዊ በደሎች እየተፈፀሙ ይገኛል። ህዝቡ የሚያሰማውን እሮሮ ለአንባቢያን ለማቅረብ፣ ዞብል ፖስት “ራያ እንዴት ከርሞ ይሆን?” በማለት የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሮ ይህንን የምርመራ ዘገባ ሠርቷል።
የምርመራ ዘገባውን ለማጠናቀር፣ የአካባቢውን ታሪካዊና ፖለቲካዊ ዳራዎች የሚዳስሱ መዛግብትን አገላብጠናል። ከዚህም በተጨማሪ፣ በአካባቢው የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቃለመጠይቅ አድርገናል። በዚህ የምርመራ ዘገባ ላይ በቃለመጠይቅ የተሳተፉ ግለሰቦች፣ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው አልተጠቀሰም።
ድህረ 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ራያ፣ ለዋናው ጉዳያችን እንደ መንደርደሪያ
ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ፣ በ1984 ዓመተ-ምህረት፣ የኢፌድሪ ህገመንግስት ከመፅደቁ በፊት፣ ህወሓት ራያ ተበሎ ከሚጠራው አካባቢ የተለያዩ ወረዳዎችን በጉልበት ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ማድረጉ ይታወቃል። አንድ የአካባቢውን ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ዳራ ጠንቅቀው የሚያውቁ በእድሜ የገፉ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ፣ “ይህ የተደረገው ህብረተሰቡን ሳያወያዩ እና ፈቃደኝነቱን ሳይጠይቁ ነው። አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የከርሰምድር ውሃ ሀብት እና ለግብርና ምቹ የሆነ ለም መሬት ያለው ስለሆነ፣ ይሄንን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም ሲሉ የራያን ህዝብ ያለፍላጎቱ ወደ ትግራይ እንዲካለል አድርገዋል።” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጋራሉ።
ከዛ ጊዜ ወዲህ የራያ አካባቢ ህዝብ ራያ አላማጣ፣ አላማጣ ከተማ፣ ራያ ባላ፣ ራያ ኮረም፣ ራያ ኦፍላ፣ እና ራያ ዛታ በሚባሉ ስድስት ወረዳዎች ላይ፣ “የራያ ወሎ አማራ የወሰንና ማንነት” ጥያቄዎችን ሲያቀነቅን ኖሯል። ይህ ህዝባዊ ጥያቄ፣ የህይወት መስዕዋትነትን እና መፈናቀልን ጨምሮ፣ ብዙዎችን ዋጋ ያስከፈለ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው ሰዎች ይገልፃሉ። ቀደም ባለው የትግል እንቅስቃሴ፣ በራያ ከተማ እና በራያ አላማጣ ዙሪያ “እኛ ወሎየዎች ነን፣ ማንነታችንም አማራ ነው፣ በመሆኑም ወደ ትግራይ መካለላችን አግባባነት ስሌለለው ወደ ትክክለኛው ማንነታችን ልንመለስ ይገባል” የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሱ የነበሩ ተሰሚነት ያላቸው እና በአካባቢው ተቀባይነት የነበራቸው ሰዎች እንዲታሰሩ፣ ታፍነው እንዲወሰዱ፣ ደብዛቸው እንዲጠፋ፣ እንዲሁም እንዲገደሉ መደረጉን፣ በቃለመጠይቁ የተሳተፉት በእድሜ ጠና ያሉት ግለሰብ ያስረዳሉ። በተመሳሳይ፣ ቀደም ብሎ በነበረው እንቅስቃሴ ወደ ትግራይ ክልል በኃይል መካለላቸውን የተቃወሙ ግለሰቦች፣ በኮረም ከተማ በአደባባይ ገበያ መሃል እንደተረሸኑ ያነጋገርናቸው ሰዎች ለዞብል ፖስት ይገልፃሉ።
የደርግን ስርዓት ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል፣ ከህወሓት ጋር ጥምረት ፈጥረው ሲታገሉ የቆዩ የራያ የነፃነት ታጋዮች ነበሩ። ሆኖም ግን፣ የኢህአዴግ መንግሥት ስልጣን ሲቆጣጠር ራያን ወደ ትግራይ ለማካለል ለታሰበው እቅድ መሰናክል ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ፣ “ሀውጃኖን” ጨምሮ አብዛኛዎቹ የነፃነት ታጋዮች በደርግ ውድቀት ዋዜማ ላይ በግፍ መገደላቸውን መዛግብት ያሳያሉ፣ ነዋሪዎችም ሁኔታውን የትናንት ያህል ያስታውሱታል። “በዚህ አይነት ሂደት፣ ህወሓት ራያን ወደ ትግራይ ለማካለል ሲል ቀድሞ መደላደል የመስራት እቅዱን አሳክቷል” በማለት ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉ የአካባቢው ተወላጅ በሰጡት ቃለመጠይቅ ያስረዳሉ።
እንዲያም ሆኖ ግን፣ ህዝቡ የማንነት ጥያቄውን ይበልጥ እያጠናከረ እና እየተደራጀ ሊሄድ ችሏል። በ2010 ዓመተ-ምህረት የአካባቢው ምሁራን “የራያ ወሎ አማራ ወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ” የተሰኘ ስብስብ አዋቅረው፣ 27,500 ገደማ ፊርማ (petition) ከህዝቡ አሰባስበው፣ በባለ 34 ገፅ ሰነድ የታገዘ የወሰን እና የማንነት ጥያቄያቸውን ለትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጥቅምት 2011 ዓመተ-አስገብተው ነበር።
“ህገመንግስቱ በሚያዝዘው መሠረት ለጥያቄያችን በሁለት ዓመት ውስጥ መልስ ሊሰጠን ሲገባ፣ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ግን ምንም አይነት ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም ነበር።” ሲሉ ቃለመጠይቅ ያደረግንላቸው የኮሚቴው አባል የትግላቸውን ዳራ ያስታውሳሉ። ይሄንን ተከትሎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት “ጥያቄያችንን በይግባኝ እንዲመለከተልን ለመጠየቅ ስንሄድ፣ በወቅቱ የምክር ቤቱ አፈጉባኤ የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ያስገባነው ሰነድ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ አድርገዋል” ሲሉ እኒሁ የወሰንና የማንነት ኮሜቴ አባል ይገልፃሉ።
በምክር ቤቱ ተገኝተው ጉዳያቸውን ሲያስረዱ፣ “የእናንተ ጥያቄ እዚህ የለም!” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው፣ በቃለመጠይቁ ላይ ተሳታፊ የነበሩ እኒሁ የራያ ወሎ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል ጉዳዩን ያስረዳሉ። በዚህ ምክንያት “ጥያቄያችን ተገቢውን ምላሽ እንዳያገኝ በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች፣ በተቀናጀ ሁኔታ ሲሰሩ ነበር” በማለት ሁነቱን ያስታውሳሉ።
<<የፕሪቶሪያው ስምምነት እና አሳዛኙ የራያ ዕጣፋንታ>>
በፌዴራል መንግስቱ እና በህወሓት መካከል በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ጦርነት፣ ህወሓት መቀሌን ለቅቆ ከወጣ በኋላ፣ በስድስቱ ወረዳዎች ማለትም፤ ራያ አላማጣ፣ አላማጣ ከተማ፣ እና ራያ ባላ በሰሜን ወሎ ስር፣ እንዲሁም ራያ ኮረም፣ ራያ ኦፍላ፣ እና ራያ ዛታ የሚባሉት ሶስት ወረዳዎች ደግሞ በዋግህምራ ስር ሆነው፣ ከታህሣሥ 2013 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ በህዝቡ በተመረጡ የአካባቢው መሪዎች በአማራ ክልል ስር ሆነው ሲተዳደሩ ነበር።
መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቅቆ ከወጣ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ፣ ራያን እና አካባቢውንም ጭምር ለቅቆ መውጣት ጀመረ። የህወሓት ታጣቂዎች አካባቢውን መልሰው መቆጣጠራቸውን ተከትሎ፣ አብዛኛው የዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ከሐምሌ 2013 እስከ መስከረም 2015 ዓመተ-ምህረት ድረስ አካባቢውን ለቅቀው በስደት በተለያዩ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ለመኖር የተገደዱበት ጊዜ ተፈጥሯል።
በነዚህ ጊዜያት በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ በአማራ ክልል በኩል የሚመጣው እስከ ቆቦ ድረስ ብቻ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል በኩል የሚመጣው እስከ መሆኒ ብቻ ይደርስ ስለነበር፣ የስድስቱ ወረዳዎች ህዝብ ለሁለት ዓመታት ያህል ለከፍተኛ ችግር ተዳርጎ ነበር። “ብዙዎች በመድሃኒት እና በመሰረታዊ የምግብ አቅርቦት እጦት ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል” ሲሉ፣ በጊዜው ከተፈናቃዮቹ አንዱ የነበሩት የቃለመጠይቁ ተሳታፊ ይገልፃሉ።
በመጨረሻው ዙር ጦርነት እስከ ጣርማበር ድረስ ገፍቶ ሄዶ የነበረው የህወሓት ሰራዊት ተሸንፎ የአማራ ክልልን ለቅቆ ከወጣ በኋላ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ግስጋሴውን ራያ ቆቦ ላይ ገትቶ ወደ ፕሪቶሪያ ስምምነት ተገባ። ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ፣ የወሰን እና ማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች ማለትም፤ ራያ አላማጣ፣ አላማጣ ከተማ፣ እና ራያ ባላ በሰሜን ወሎ ስር፣ እንዲሁም ራያ ኮረም፣ ራያ ኦፍላ፣ እና ራያ ዛታ ደግሞ በዋግህምራ ስር ሆነው በአማራ ክልል ስር እየተዳደሩ፣ ጉዳያቸው መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ የፌደራል መንግሥት ኃይሎች በአካባቢው ይቆያሉ ቢባልም፣ በሚያዚያ 7፣ 2016 ዓመተ-ምህረት፣ ህወሓት እነዚህን የወሰን እና ማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በኃይል ተቆጣጥሮ ሊይዝ ችሏል።
የህወሓት ታጣቂዎች እነዚህን ወረዳዎች በኃይል ከመቆጣጠራቸው በፊት፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት በራያ አዘቦ እና ራያ አላማጣ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰፍረው ነበር። በዚህ ምክንያት፣ “የፌዴራል መንግሥት የህወሓት ታጣቂዎች አካባቢውን እንዲቆጣጠሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል የሚል ግምት አልነበረንም” ሲሉ ሌላኛው ቃለመጠይቅ ያደረግንላቸው ግለሰብ ይገልፃሉ። ሁነቱን፣ “የዐቢይ አህመድ መንግሥት የፈፀመብን ታላቅ ክህደት” ሲሉ አያይዘው ገልፀውታል።
ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም ወዲህ ያለው የአካባቢው ሁኔታ ምን ይመስላል?
የህወሓት ታጣቂዎች እነዚህን አካባቢዎች በኃይል ከተቆጣጠሩ ባለፈው ሚያዚያ አንድ ዓመት ሞልቶታል። የህወሓት ታጣቂዎች አካባቢውን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ፣ ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ወዲያውኑ መፈናቀላቸውን እና ቆቦ እና ሰቆጣ በሚገኙ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ማረፋቸውን፣ United Nations Office for the Coordination of Humanitarian Affairs (OCHA) ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ቀስ በቀስ ራያ ባላ፣ ራያ ኦፍላ፣ እና ራያ ዛታ ገጠራማ አካባቢዎች፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በህወሓት ሠራዊት ቁጥጥር ስር መውደቃቸውን በቆቦ የተፈናቃዮች ጣቢያ የነበሩ ግለሰብ ያስረዳሉ። የህወሓት ታጣቂዎች፣ በአላማጣ እና ኮረም ከተሞች በአንድ የሙያ እና ቴክኒክ ተቋም፣ እንዲሁም በአምስት ትምህርት ቤቶች ላይ፣ የጦር ሰፈሮችን ሰርተው እንደሚገኙ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማህበራዊ በደል እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ይናገራሉ። የህወሓት ታጣቂዎች፣ “ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ያሏቸውን ሰዎች በምሽት ቤታቸው ድረስ ሄደው አፍነው ወዳልታወቀ ስፍራ ወስደው ያስራሉ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ድብደባ በመፈፀም በየአጥሩ ስር ጥለዋቸው ይሄዳሉ” ሲሉ ኑሯቸውን በአላማጣ ከተማ ያደረጉ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ ግለሰብ ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ በአብዛኛውን ጊዜ ከምሽት ሁለት ሰዓት ጀምሮ የህወሓት ታጣቂዎች የምሽት ቅኝት ስለሚያደርጉ፣ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ እና ድብደባ እንደሚፈፅሙ አስረድተዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የህወሓት ታጣቂዎች “ትምህርት ቤቶችን ለቅቀው እንዲወጡ እና ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ” ሠላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ነዋሪዎች ላይ፣ ታጣቂዎቹ ተኩስ ከፍተው ንፁሃን ተገድለዋል ብዙዎች ለከፋ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል።
ለአብነት ያህል፣ በሠላማዊ ሰልፍ ላይ በተከፈተ ተኩስ፣ በአላማጣ ከተማ 07 ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አቶ አበራ የተባሉ የሶስት ልጆች አባት፣ እንዲሁም የ08 ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አቶ ኃይሉ አሸበር የተባሉ የሁለት ልጆች አባት፣ በጥይት መገደላቸውን፣ ከአስር በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በቃለመጠይቁ የተሳተፉ የአይን እማኝ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
“መንግሥት አልባ ህዝብ ሆነናል”
ከሚያዚያ 7፣ 2016 ዓመተ-ምህረት አንስቶ፣ ራያ እና አካባቢው ላይ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንቅስቃሴ ማቆማቸውን፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች በከፍተኛ ሁኔታ መስተጓጎላቸውን፣ እና ትምህርት ቤቶች የጦር ካምፕ መደረጋቸውን በዚህ የምርመራ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
በአካባቢው የተቋቋመው በኮሎኔል አህመድ የሚመራው የኮማንድ ፖስት፣ የህወሓት ታጣቂዎች የሚፈፅሙትን በደል የማስቆም፣ ህዝቡ ለሚያቀርባቸው አቤቱታዎች ምላሽ የመስጠት፣ በአጠቃላይ የአካባቢውን ሠላም እና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባራቶችን ከማወከናወን መታቀቡን ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ። ይባስ ብሎም፣ ድምፃቸው እንዲሰማ የሚጠይቁ የአካባቢው ነዋሪዎች “የፋኖ ደጋፊ ናችሁ” ተብለው በመከላከያ ሰራዊቱ ድብደባ እና እስር እንደሚፈፀምባቸው፣ ይህንን የምርመራ ዘገባ ለማጠናቀር ካነጋገራቸው ግለሰቦች ለመረዳት ተችሏል። በዚህ የምርመራ ዘገባ፣ የኮማንድ ፖስቱን ሃላፊ ምላሻ ለማካተት በሚል፣ ኮሎኔል አህመድን ለማናገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
የነዋሪዎቹን የየለት እሮሮ ችላ ከማለት በተጨማሪ፣ በአካባቢው ሰፍሮ የሚገኘው የፌዴራል መንግሥት ሠራዊት፣ ነዋሪዎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ግፎችን እንደሚፈፅም፣ በምርመራ ዘገባችን ለመረዳት ችለናል። ለአብነት ያህል፣ በየካቲት 28፣ 2017 ዓመተ-ምህረት፣ ለአርባ ዓመታት የዜማና የቅኔ መምህር ሆነው ያገለገሉ አይነ-ስውሩ መምህር አባ ገብረመድህን እና አራት ዲያቆናት፣ ያገለግሉበት ከነበረው የሰሜን ወሎ ዞን፣ ራያ ጥሙጋ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አቅራቢያ፣ በፌዴራል መንግስት ወታደሮች በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። አስር የሚሆኑ የቆሎ ተማሪዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።
በቃለመጠይቁ ተሳታፊ የሆኑ አንድ ልጃቸው ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመበት ግለሰብ “እየኖርን ያለነው በፈጣሪ ቸርነት ብቻ ነው። የህወሓት ታጣቂዎችም ሆነ በኮማንድ ፖስቱ ስምሪት ተሰጥቷቸው የሚገኙ የመንግስት ኃይሎች፣ አግተው ቢወስዱን ወይም በመንገድ ላይ ገድለው ቢጥሉን፣ የሚደርስልን አካል የለም” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ በምሬት ያስረዳሉ።
በቃለመጠይቁ የተሳተፉ አንድ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ፣ “ጠያቂ እና ተመልካች ያጣንበት፣ ከኢህአዴግ ዘመን በከፋ የጨለማ ዘመን ውስጥ እየኖርን ያለንበት ጊዜ ነው” ሲሉ ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ ይገልፃሉ። እኚህ ግለሰብ በንግድ ስራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበረ ሲሆን፣ ባሳለፍነው መስከረም ወር በህወሓት ታጣቂዎች ዝርፊያ የተፈፀመባቸው ናቸው።
የህወሓት ታጣቂዎች በሚያዚያ 2016 ዓመተ-ምህረት አካባቢውን ሲቆጣጠሩና የአካባቢው አስተዳደር ሲፈርስ፣ በስሩ የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሚሊሻዎች ቀድሞ የምስራቅ አማራ ፋኖ ተብሎ ይጠራ የነበረውን የፋኖ ኃይል መቀላቀላቸው ተዘግቦ ነበር። ይሁንና፣ ወደ ፋኖ ተቀላቅለዋል የተባሉት ታጣቂዎች፣ ህወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ያን ያህል እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዳልቻሉ፣ ያነጋገርናቸው የአላማጣ እና አካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
በአካባቢው በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችሉት እና ያሻቸውን እያደረጉ ያሉት፣ የህወሓት ታጣቂዎች መሆናቸውን በማውሳት “የፌዴራል መንግሥትም ሊደርስልን አልቻለም፣ ጉዳያችንን እስከ ርዕሰ-መስተዳድር ቢሮ ብናደርስም፣ የአማራ ክልል መንግሥት ተፀዕኖ መፍጠር የማይችልና ደካማ በመሆኑ፣ ያለንበትን ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት አልቻለም” ሲሉ፣ አንድ ይሄንን ዘገባ ለማጠናቀር በቃለመጠይቁ የተሳተፉ ግለሰብ ያስረዳሉ።
የአካባቢው ህዝብ “በዚህ ሁኔታ እስከመቼ እንቀጥላለን” የሚል ጭንቀት እንዳደረበት እኒሁ ግለሰብ ያስረዳሉ። “ለማን እንደምንጮህ አናውቅም። ልክ እንደ ነፍሰ ጡር ቀን በመቁጠር ነው ጊዜያችንን የምናሳልፈው” ሲሉ፣ ከራያ አላማጣ ተሰድደው ኑሯቸውን በወልድያ ከተማ ያደረጉ እናት ስሜታቸውን አጋርተውናል።
የራያ ጉዳይ እና የሚዲያዎች ዝምታ
ከሚያዚያ 2016 ዓመተ-ምህረት ወዲህ ያለው የራያ እና አካባቢው ሁኔታ፣ “ህዝቡ እያለፈበት ባለው ስቃይ ልክ የሚዲያ ሽፋን እያገኘ እንዳልሆነ” ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያደርጉ ግለሰቦች ቅሬታቸውን አቅርበዋል። አንድ በራያ ወሎ አማራ ማንነት እንቅስቃሴ የሚሳተፉ ግለሰብ፣ “እያለፍንበት ላለው አሳሳቢ ሁኔታ ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን የሚሰጠን የሚዲያ አካል አጥተናል” በማለት የሚዲያዎችን ቸልተኝነት ኮንነዋል።
በተመሳሳይ፣ “ለብዙ የሚዲያ ባለቤቶች እና ጋዜጠኞች ድምፅ እንዲሆኑን በየጊዜው ብንጠይቅም፣ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም” ሲሉ ቅሬታ አዘል መልስ ጨምረው ሰጥተዋል። በማህበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ አንድ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ፣ በአማራ ስም የተቋቋሙ እንዲሁም ሌሎች የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች፣ የራያን ችግር ትኩረት እንዲሰጡት ጥሪ አቅርበዋል።
ባሳለፍነው የትንሳዔ በዓል ምሽት፣ በአላማጣ ከተማ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ታላቅ ወንድሟ ወደ ቤቱ እያቀና በነበረበት ሰዓት፣ በመንገድ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞበት፣ ተጎጅውን ወንድሟን በወልዲያ ከተማ በሚገኝ የህክምና ጣቢያ በማስታመም ላይ ያለች የዩኒቨርስቲ ተማሪ በበኩሏ፣ “ወንድሜን ጨምሮ ንፁሃን በየጊዜው ድብደባ ይፈፀምባቸዋል፣ ታፍነው ይወሰዳሉ፣ የሞቱም አሉ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ተቋማት፣ እንዲሁም የሚዲያ አካላትና ጋዜጠኞች፣ ያለንበትን ሁኔታ እባካችሁ ትኩረት ስጡት” ስትል የተማፅኖ መልዕክት አስተላልፋለች።
መጪው የራያ ዕጣ ፋንታ እና የተጋረጡ ስጋቶች፣ እንደ ማጠቃለያ
ከነገሮች ለመረዳት እንደሚቻለው፣ የፌደራል መንግስቱ ራያ እና አካባቢው የውዝግብ ቀጠና ሆኖ እንዲቀጥል የሚፈልግ ይመስላል። መንግሥት የወሰን እና ማንነት ጥያቄ ለሚነሳባቸው አካባቢዎች ተገቢውን መፍትሔ በመስጠት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል ያሉ ቅራኔዎች እልባት እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ፣ “የውዝግብ አዙሪቱ እንዲቀጥል ሊያደርግ ይችላል” የሚል ስጋትን በብዙሃኑ ዘንድ አሳድሯል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ከፍተኛ መከፋፈል ምክንያት፣ የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት (የአሁኑ የጠቅላይ ሚንስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ) የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ቡድናቸው፣ በራያ እና አካባቢው ፖለቲካ የኃይል ሚዛን ብልጫ እንዲወስዱ የፌደራል መንግሥቱ ተባባሪ ሆኗል ተብሎ ይታሰባል። ይህ ሁኔታ የዐቢይ አህመድ መንግሥት “የራያን ጉዳይ” በይደር በማስቀመጥ የትግራይን ፖለቲካ ለመቆጣጠር እቅድ እንዳለው ያመላክታል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በግንቦት 6፣ 2017 ዓመተ-ምህረት ህወሓት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን ተከትሎ፣ ጉዳዩ ሌላ ዙር ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የተለያዩ ወገኖች ሃሳባቸውን በማጋራት ላይ ይገኛሉ። ይህ ስጋት እውን የሚሆን ከሆነ ደግሞ፣ በራያ እና አካባቢው የሚኖረው ህዝብ ከዚህ በፊት ካለፈባቸው አደጋዎች የከፋ አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል ይገመታል። ሁኔታውን “እጅግ አስፈሪ እና እንቅልፍ የሚነሳ ነው” ሲሉ፣ ዞብል ፖስት ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ሁኔታውን በጭንቀት ይገልፁታል።