ሰኔ 5/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት የአፍሪካ ቀንድ ዜና
ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ሁለቱን ሀገራት ለማቀራረብ እንቅስቃሴ መጀመሯን፣ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ መስከረም 2018 ዓ.ም በዐቢይ አህመድ እና ኢሳያስ አፈወርቂ በተፈረመው “የጅዳው የሠላም ስምምነት” ሳዑዲ አረቢያ ሁለቱን ሀገራት እርቅ እንዲፈፅሙ ማድረጓ የሚታወስ ሲሆን፣ ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለሃያ ዓመታት የቆየው የግጭት አዙሪት ወደ ሠላማዊ ግንኙነት መቀየሩ ይታወሳል።
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ፣ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ውጥረት እየነገሰበት መምጣቱ ይስተዋላል። ጉዳዩ አሳስቦኛል ያለችው ሳዑዲ አረቢያ ይሄንኑ ውጥረት ለማርገብ ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ መጀመሯን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
የሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑን ፈይሰል ቢን ፋራህ አል-ሳዑድ የኢትዮጵያን እና ኤርትራን ባለስልጣናት ለማነጋገር ጥረት መጀመራቸውን፣ ሁኔታውን አስመልክቶ ለመፅሔታችን መረጃውን ያደረሱ የዲፕሎማቲክ ምንጮች አስረድተዋል።
ሳዑዲ አረቢያ ከሰባት ዓመታት በኋላ ድጋሚ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን ለማቅራረብ እንቅስቃሴ መጀመሯ፣ ሀገሪቷ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እና በቀይ ባህር ከባቢ ፖለቲካ ላይ ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።
ሳዑዲ አረቢያ ሁለቱን ሀገራት ለማነጋገር እንቅስቃሴ ጀምራለች ቢባልም፣ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ መንግሥታት በኩል እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የተሰጠ ምላሽ የለም።