ሰኔ 7/2017 ዓ.ም – ዞብል ፖስት የምርመራ ዘገባ!
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ በአዲስአበባ እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየተገነቡ በሚገኙ እና ተገንብተው በተጠናቀቁ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ እንዳላቸው ዞብል ፖስት ከምንጮቹ ሰምቷል።
ለአብነት ያህል፣ ሰሞኑን የኢትዮጵያን የመጠጥ ገበያ ከተቀላቀለው ኬኛ ቢራ ፋብሪካ፣ 45 ፐርሰንት ያህሉ ድርሻ የሽመልስ አብዲሳ እንደሆነ የዞብል ፖስት ምንጮች ጠቅሰዋል። ፋብሪካውን ለመገንባት 250 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን፣ አቶ ሽመልስ የአክሲዮን ድርሻቸውን ለመሸፈን ከሲንቄ ባንክ ከፍተኛ ገንዘብ እንደወሰዱ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በሞጆ እና ናዝሬት ከተሞች መካከል በሚገነባው የኢንዱስትሪ፣ የንግድ፣ የቴክኖሎጂ፣ እና የኢንቨስትመንት ከተማ ከሆነው “ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን” ውስጥ፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከቻይና ባለሀብቶች ጋር በሽርክና ለመስራት ምስጢራዊ ውል መፈራረማቸውን ዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በሌላ በኩል፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአዲስአበባ ተገንብተው በተጠናቀቁ እና በመገንባት ላይ ባሉ በርካታ የገበያ ማዕከሎች እና ሪልስቴቶች ላይም፣ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ እጅ እንዳለበት ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
አቶ ሽመልስ በእነዚህ የገበያ ማዕከሎች ላይ ያላቸው ድርሻ በቅርብ ቤተሰቦቻቸው የተያዘ ስለመሆኑ ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል። መረጃውን ለመፅሔታችን ያደረሱት ምንጫችን፣ “ሽመልስ አብዲሳ የኢኮኖሚ ኢምፓየር እየገነባ ነው” በማለት ሁነቱን ይገልፁታል።
ሌላኛው የዞብል ፖስት ምንጭ ባደረሱን መረጃ መሰረት ደግሞ፣ ሽመልስ አብዲሳ በቅርቡ በተመሰረተው ሸገር ሲቲ ውስጥ በቅርብ ቤተሰቦቹ ስም ከ40 በላይ ቦታዎች ታጥረው እንዲቀመጡ ማድረጋቸው ተሰምቷል። ቦታዎቹን ለቤቶች ልማትና ለጨረታ እያዘጋጇቸው መሆኑንም የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልፀዋል።
በሌላ መረጃ፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሜድሮክ ወርቅ ኩባንያን ከሼህ መሐመድ አላሙዲን ለመንጠቅ ሙከራ አድርገው እንደነበር እና እቅዳቸው ለጊዜው እንዳልተሳካ ዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ከሀብት ምንጫቸው ባሻገር፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የመሆን ህልም እንዳላቸውም ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል። ለዚህም እንዲረዳቸው የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮችን በጥቅም ትስስር ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
አቶ ሽመልስ በተደጋጋሚ ከሚያደርጓቸው አስገራሚ ነገሮች መካከል፣ ለአዲስ ዓመት፣ ለመስቀል፣ ለኢሬቻ፣ ለገና፣ ለፋሲካ፣ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት በሚያዘጋጃቸው በዓላት ወቅት፣ ለመከላከያ ጄኔራሎች እንደየ ማዕረጋቸው የሚለያይ ለእያንዳንዳቸው ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ዶላር በስጦታ መልክ እንደሚሰጡ ዞብል ፖስት ያገኘው መረጃ ያሳያል።