ሰኔ 10/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
በአዲስአበባ የሚኖሩ በርካታ ኤርትራውያን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው የመረጃ ምንጮች ሰምቷል።
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረኃይል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረጉትን ኤርትራውያንን ጉዳይ በዋነኛነት እንዲይዝ የተደረገ ሊሆን፣ በዚሁ ግብረኃይል ክትትል መሰረት በመዲናዋ የሚኖሩ በርካታ ኤሪትሪያውያን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዞብል ፖስት ከምንጮቹ ሰምቷል።
በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል የተባሉት ኤርትራውያን ለሻዕቢያ በስለላ ተግባር ተሰማርተዋል እንዲሁም በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ መሆናቸውን ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የመረጃ እና ደህንነት ዋና ኃላፊ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረኃይሉን እንዲያስተባብሩ እና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሚደረጉ ኤርትራውያንን ጉዳይ በዋናነት እንዲቆጣጠሩ መመደባቸውንም ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
ከኤርትራውያን እስር ጋር በተያያዘ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ በሁለት አካባቢዎች ወታደራዊ ስልጠና መጀመሩ የተነገረለት ብርጌድ ንሓመዱ አመራሮች እና አባላት፣ ለፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረኃይሉ መረጃ በመስጠት ተባባሪ መሆናቸውን ዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግንኙነታቸው መሻከሩን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በርካታ ኤርትራውያንን በቁጥጥር ስራ ማዋላቸው ውጥረት የነገሰበትን የኢትዮጵያ እና ኤርትራን ግንኙነት ሊያባብሰው እንደሚችል ይገመታል።