ሰኔ 10/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት አራት ኪሎ!
በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው እና መርማሪዎችን ከሞት በስተቀር ተጠያቂ አያስደርግም የተባለው በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን የሚመለከት አዋጅ፣ ለሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለው አንድምታ እጅግ አስደንጋጭ ነው።
አዋጁ ሽብርተኝነትን እና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ያለመ ነው ተብሎ ቢገለጽም፣ ከአዋጁ ጀርባ ያለው የአገዛዙ ፍላጎት ግን የሕግ የበላይነትን፣ የዜጎችን ደህንነት እና የመናገር ነፃነትን በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ላይ የሚጥል ነው።
አዋጁ የኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ ክብር የሚያዋርድ እና በወንጀል ምርመራ ስም የጭካኔ ድርጊቶችን (undercover investigation) ለመፈፀም ያለመ ነው። ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጸም ማንኛውም ወንጀል መርማሪዎች ተጠያቂ እንደማይሆኑ የሚገልፀው ይህ አዋጁ፣ የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር የሚጨፈልቅ እና ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶችን በነፃነት ለመፈፀም የሚያስችል መንግሥታዊ ወንጀልን ሕጋዊ የሚያደርግ አዋጅ ነው።
በምርመራ ወቅት መርማሪዎች ከግድያ ውጭ ያሉ የምርመራ ዘዴዎችን እንዲፈፅሙ የሚፈቅደው ሕግ፣ ምርመራ የሚደረግባቸው ተጠርጣሪዎችን አካል ማጉደል እና ማሳቃየትን ሕጋዊ ሽፋን የሚሰጥ አዋጅ ነው። ሁኔታውም የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በቀጥታ የሚጥስ ነው።
አዋጁ ሲተረጎም፤ በወንጀል ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የሚገኙ ዜጎች፣ በመርማሪዎቹ ተዘቅዝቀው ቢገረፉ፣ ጥፍራቸው ቢነቀል፣ አይናቸው ቢጠፋ፣ አካላቸው ቢጎድል፣ የመራቢያ አካላቸው ከጥቅም ውጭ ቢሆን፣ የአስገድዶ መድፈር እና ግብረሰዶማዊ ጥቃት ቢፈፀምባቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ እስካልሞቱ ድረስ መርማሪዎቹ ያሻቸውን ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው።
አዋጁ ኢትዮጵያ ፈራሚ የሆነችባቸውን የዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ በተለይም ዜጎችን በምርመራ ወቅት የማሰቃየትን፣ ጭካኔ የተሞላባቸው ኢሰብዓዊ እና አዋራጅ አያያዞችን፣ እንዲሁም ቅጣቶችን የሚከለክሉ ስምምነቶችን በሙሉ መርማሪዎች እንደፈለጋቸው መጣስ እንዲችሉ የሚፈቅድ ሕግ ነው።
ይህ አዋጅ፣ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ፣ ዐቢይ አህመድ በጸጥታ ኃይሎቹ በኩል ጭካኔ የተሞላበት ፈላጭ ቆራጭ የሆነ ሥርዓትን በሕግ ከለላ ለመገንባት ቆርጦ የተነሳ መሆኑን በግልፅ የሚያመላክት ነው።
አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሕግ ከለላ ከመስጠት ባሻገር፣ በእጅጉ የጠበበውን የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እና የፖለቲካ ምህዳር ጨርሶ የሚያጨልም እና የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነት፣ የመናገር ነፃነት፣ እና የፖለቲካ ተሳትፎ ከኢትዮጵያ ምድር ፈፅመው እንዲጠፉ ለማድረግ አገዛዙ ግልፅ እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚያሳይ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ አዋጁ የሽብርተኝነትን እና የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ትርጓሜ ከልክ በላይ በማስፋት፣ ከስደት የተረፉትን የተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ እና ባለሀብቶች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚጥልና ተሸማቅቀው እንዲኖሩ የሚያደርግ ፀረ-ሰው አዋጅ ነው።
ይህ ሁሉ የሚያሳየው፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ከሁሉም የተቃዋሚ ድምጾች በማፅዳት፣ ያልተገደበ ስልጣንን ለመያዝ፣ እና የሞራልና የሕግ ገደቦችን በኃይል ለመጨፍለቅ መዘጋጀቱን እና ስልጣኑን ለረዥም ጊዜ በኃይል ለማስቀጠል በመስራት ላይ እንደሚገኝ ነው።
የአዋጁ ሌላው አሳሳቢ ገጽታ፣ አዋጁ ከፀደቀበት ጊዜ በፊት ለተፈጸሙ ድርጊቶች ጭምር ተግባራዊ ሊሆን ይችላል መባሉ ነው። ይህ ከሆነ፣ የሕግን የኋላ ታሪክ ተፈጻሚ ያለመሆን መርህን የሚጥስ ነው።
ድንጋጌው ከፍተኛ የፍትህ መጓደልን ከማስከተሉም በላይ፣ መንግሥት የተወሰኑ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ሆን ብሎ ኢላማ በማድረግ፣ ሕግን ለበቀል መሳሪያ ለመጠቀም ማሰቡን ያሳያል። ይህ የሚሆን ከሆነ ደግሞ፣ መንግሥት ከዚህ ቀደም እስር ቤት በወረወራቸው የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ላይ አሰቃቂ ተግባራትን ሊፈፅም ይችላል።
የዐቢይ አህመድ መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ያደረገው አዋጅ በግልፅ ቋንቋ ሲተረጎምም፣ እነዚህን እና መሰል ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ሕጋዊ ሽፋን የሚሰጥ ነው።