Thursday, June 19, 2025

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዘገባዎችየምርመራ ዘገባሙስና እና ኮንትሮባንድ የተንሰራፋበት የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር! 

ሙስና እና ኮንትሮባንድ የተንሰራፋበት የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር! 

ሰኔ 11/2017 ዓ.ምዞብል ፖስት የምርመራ ዘገባ!

ባሳለፍነው ሐምሌ 2016 ዓ.ም ኢንጅነር ታከለ ዑማ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ከተሾሙ ጊዜ አንስቶ፣ በተቋሙ ውስጥና በባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሙስና እና የኮንትሮባንድ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ኢንጅነር ታከለ ዑማ ከዚህ ቀደም ሕግን ባልተከተለ መልኩ በዐቢይ አህመድ አማካኝነት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ተደርገው በተሾሙበት ጊዜ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይም በሕገ-ወጥ የመሬት ሽያጭ እና ዕደላ ጉዳይ ስማቸው ከሙስና ጋር በተደጋጋሚ ሲነሳ እንደነበር ይታወሳል።

ምክትል ከንቲባ ተደርገው በተሾሙበት ወቅት በኢንጅነር ታከለ ዑማ ላይ ይቀርብ የነበረው የሙስና ቅሬታ፣ አሁን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው በተሾሙበት በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ውስጥ ለሙስና እና ኮንትሮባንድ ንግድ መንሰራፋት እንደ ቅድመ-ግንዛቤ ሊወሰድ ይችላል።

ለሙስና እና ኮንትሮባንድ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በሚል፣ ኢንጅነር ታከለ ዑማ የተቋሙን የአመራር እና መዋቅራዊ ቦታዎችን በራሳቸው ቀጥተኛ ትዕዛዝ መልሰው የማደራጀትና አዳዲስ ሰዎችን በኃላፊነት የመመደብ ስራዎችን ቀድመው ማከናወናቸውን ዞብል ፖስት ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጧል። ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ታከለ ዑማ፣ ቤተሰቦቻቸው፣ እና የቅርብ ዘመዶቻቸው ተቋሙን ተጠቅመው ከፍተኛ ሀብት እያፈሩበት ይገኛሉ።

ኢንጅነር ታከለ ዑማ አዳዲስ ሰዎችን በኃላፊነት የመመደብ ስራዎችን ቀድመው ማከናወናቸውን ተከትሎ፣ አክሲዮን ማህበሩ 7 የስራ አስፈፃሚ አባላት ያሉት ሲሆን፣ በኢንጅነር ታከለ ዑማ ትዕዛዝ መሰረት ስድስቱ የስራ አስፈፃሚ አባላት የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ እንዲሆኑ መደረጉን በተቋሙ ውስጥ የሚሰሩ የመረጃ ምንጫችን ለመጽሔታችን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር 59 ዳይሬክተሮች ያሉት ሲሆን፣ ኢንጅነር ታከለ ዑማ በዋና ስራ አስፈፃሚነት ከተሾሙ ወዲህ 49ኙን የዳይሬክቶሬት ሃላፊዎች የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ማድረጋቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የመረጃ ምንጫችን አስረድተዋል።

ይህንን አሰራር ተገቢ አይደለም ብለው የተቃወሙ 9 የሌላ ብሔር ተወላጅ ነባር መሐንዲሶች ከስራ እንዲባረሩ እና እንዲታሰሩ ተደርገዋል። ለመጽሔታችን መረጃውን ያደረሱት ምንጮች እንዳሉት፣ በኢንጅነር ታከለ ዑማ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ከስራ ገበታቸው የተባረሩት ዘጠኙ ነባር መሐንዲሶች የታሰሩት ቡራዩ ውስጥ በሚገኝ በኢንጅነር ታከለ ዑማ የግል እስር ቤት ውስጥ ነው።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር በከፍተኛ የሙስና እና የኮንትሮባንድ ንግድ መዘፈቁን ተከትሎ፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያን እና ቀረጥ ያልተከፈለባቸውን የቀንድ ከብቶችን፣ ማሽነሪዎችን፣ ቅንጡ መኪኖችን ጨምሮ፣ ኢትዮጵያን እና ጅቡቲን በሚያገናኘው የባቡር ትራንስፖርት ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድ እንደሚተላለፍበት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጫችን ለመፅሔታችን አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ኢንጅነር ታከለ ዑማ የማዕድንና ኢነርጂ ሚንስትር እያሉ የነበራቸው የጥቅም ትስስር ተጠቅመው፣ በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናትን በኮንትሮባንድ እንደሚያጓጉዙ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ኢንጅነር ታከለ ዑማ ከኦነግ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት ፈጥረው በወለጋ አካባቢ የሚወጣውን ወርቅ በዚሁ የኢትዮ-ጅቡቲ መስመር እንደሚያጓጉዙ ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች መረጃ ደርሶታል።

የመረጃ ምንጫችን አያይዘው፣ ከዚህ ቀደም የኦነግ ታጣቂዎች የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ላይ ጥቃት ፈፅመው እንደሚያውቁ በማስታወስ፣ “ጥቃቱን የፈፀሙት ከዚህ በፊት በኮንትሮባንድ እንዲወጣ ከተደረገው ወርቅ ላይ ከተገኘው ገቢ ለኦነግ ቃል የተገባለትን ያህል ድርሻ ስላልተሰጠው ነበር” በማለት ለመፅሔታችን አስረድተዋል። 

በዚሁ የኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ፣ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን ብርሃኑ ፀጋዬን ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት ጄኔራሎች እና የመንግሥት ባለስልጣናት በጥቅም ትስስር እንደሚሳተፉ ዞብል ፖስት በጉዳዩ ዙሪያ ባደረገው ማጣራት ለማወቅ ችሏል።

የኮንትሮባንድ ንግድ ሂደቱ ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ እና ተጠያቂነት የሌለበት እንዲሆን ለማድረግ ሲባልም፣ የባቡር ጣቢያዎቹ የፍተሻና ቁጥጥር ኬላዎች በታከለ ዑማ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ እንዲመደቡበት መደረጉን ለመጽሔታችን የደረሱት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚህም በተጨማሪ፣ በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት የመንገደኞች እና የእቃ ጫኝ ባቡሮች ላይ ብልሽት ሲፈጠር፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ መቆራረጥ ሲከሰት፣ እና የቴክኒክ ጥገና ሲያስፈልግ፣ የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ታከለ ዑማ ስራዎቹን ያለምንም ጨረታ ለቻይኖች እንደሚሰጡና ከዚህም ከፍተኛ ገንዘብ በሽርክና እንደሚያገኙ መጽሔታችን ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ለመንግሥት በሚያቀርበው ሪፖርት አትራፊ ነኝ የሚል ቢሆንም፣ የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች ግን ተቋሙ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ለመጽሔታችን አስረድተዋል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች