ከሁለት ዓመታት በፊት፣ “የፋኖ ደጋፊዎች ናችሁ ወይም ፋኖ የሆኑ ዘመዶች አሏችሁ” ተብለው የታሰሩ በርካታ የመከላከያ ሠራዊት የጦር መኮንኖች እና አባላት መኖራቸው፣ በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር ነበር። ይሄንን ተከትሎ፣ ዞብል ፖስት “ለመሆኑ እነዚህ የጦር መኮንኖች እና የሠራዊቱ አባላት የታሰሩት የት ነው?” በሚል፣ ከሰሞኑ የማጣራት ስራ አከናውኗል።
በጉዳዩ ላይ ባዳረግነው ማጣራት፣ ቀጥተኛ መረጃ ያላቸውን እና ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ወታደራዊ ምንጮችን አነጋግረናል። ላነጋገራቸው ወታደራዊ ምንጮች ደህንነት ሲባል፣ በዚህ የምርመራ ዘገባ ላይ ማንነታቸው አልተገለፀም።
በአማራ ክልል ይፋዊ ጦርነት ከታወጀ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። የዐቢይ አህመድ መንግሥት ጦርነቱን ከማወጅ ጎን ለጎን፣ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በተለያዩ ኮሮች ተመድበው የነበሩ የጦር መኮንኖችን፣ አመራሮችን፣ አዋጊዎችን፣ እንዲሁም የሠራዊቱ አባላትን “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ እንዲሁም ፋኖን የተቀላቀሉ ቤተሰቦች አሏችሁ” ተብለው ከተለያዩ ዕዞች እና ክፍለጦሮች ተሰብሰበው እንዲታሰሩ ተደርጓል።
እነዚህ የአማራ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ፋኖን ለተቀላቀሉ ቤተሰቦቻችሁ ወታደራዊና ምስጢራዊ መረጃዎችን ታሾልካላችሁ” ተብለው የታሰሩ ናቸው።
ለመሆኑ እስረኞቹ የሚገኙት የት ነው?
እስረኞቹ “እንዴት እና የት ታሰሩ” ለሚለው የዞብል ፖስት ጥያቄ ምላሽ ከሰጡ የመረጃ ምንጮች አንደኛው፣ “ከሁለት ዓመታት በፊት አብዛኛዎቹ የሠራዊቱ ወታደራዊ መኮንኖች እና አባላት፣ በመጀመሪያ በጅምላ የተወሰዱት “23 45” የሚል የኮድ መጠሪያ ወዳለው፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ፓዊ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ የጨለማ እስር ቤት ነበር” በማለት ያስረዳሉ።
እኒሁ የመረጃ ምንጫችን አያይዘው፣ ከመከላከያ ሠራዊቱ እየተለቀሙ የተያዙት እስረኞች፣ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ “በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍለ-ሀገራት በሚገኙ ሌሎች እስር ቤቶች ተወስደዋል” ይላሉ።
“ለፋኖ ወታደራዊ መረጃዎችን ትሰጣላችሁ” ተብለው የተጠረጠሩ የአማራ ተወላጅ የሆኑ በርካታ የሠራዊቱ አባላት፣ በተለያዩ ወታደራዊ እስር ቤቶች ውስጥ በግፍ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ለዞብል ፖስት መረጃ ካደረሱን አካላት የተገኘው ምላሽ ያሳያል።
ስማቸው ከፋኖ ጋር ተያይዞ ለእስር የተዳረጉ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች እና አባላት፣ ከወታደራዊ እስር ቤቶች በተጨማሪ፣ መንግሥት በስውር ባዘጋጃቸው የጨለማ እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ ዞብል ፖስት ያደረገው ማጣራት ያሳያል።
በተለያዩ ክፍለ-ሀገራት ወደሚገኙ እስር ቤቶች ተወስደዋል የተባሉት የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአሶሳ፣ በጋምቤላ፣ በወለጋ፣ በአርባምንጭ፣ በአፋር፣ በደብረዘይት፣ እና ጅግጅጋ እንዲሁም፣ በሌሎች ተመሳሳይ እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ ለመፅሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ለእስር ከተዳረጉት የመከላከያ ሠራዊቱ መኮንኖች እና አባላቶች መካከል፣ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የነበሩ የሠራዊቱ አባለት ጭምር እንደሚገኙ፣ ሌላኛው የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጭ ገልፀዋል።
ከሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተይዘው የታሰሩ አብዛኛዎቹ የአማራ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ አዋሽ አርባን ጨምሮ፣ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች ባሉ ወታደራዊ እስር ቤቶች ታስረው እንደሚገኙ፣ በዚህ ዙሪያ መረጃ የሰጡን ወታደራዊ ምንጫችን ጠቁመዋል።
ጉዳዩን ለማጣራት ባደረግነው ጥረት፣ ከመከላከያ ሠራዊት አባላት በተጨማሪ፣ በርካታ የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስአበባ ፖሊስ አባላት የነበሩ የአማራ ተወላጆች፣ “ለፋኖ ድጋፍ ያደርጋሉ፣ እንዲሁም የከተማ ጥቃቶች እንዲፈፀሙ መረጃ በማቀበል ተባባሪ ናቸው” ተብለው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ታስረው እንደሚገኙ፣ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ወገኖች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።
ከአማራ ተወላጆች በተጨማሪ ያሉ እስረኞች
ከአማራ ተወላጆች የመከላከያ ሠራዊት አባላት በተጨማሪ፣ በድብቅ እና በወታደራዊ እስር ቤቶች ውስጥ፣ ሌሎች በርካታ እስረኞች እንደሚገኙ፣ ዞብል ፖስት ከዋነኛ ጉዳዩ ጎን ለጎን ያደረገው ማጣራት ያሳያል።
ለአብነት ያህል፣ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የጨለማ እስር ቤት ውስጥ፣ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ እያሉ ተይዘው ከታሰሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር አብረው ታስረው የሚገኙ በርካታ የሶማሌ ተወላጆች መኖራቸውን፣ ዞብል ፖስት ያናገራቸው የፌዴራል ፖሊስ አባል አስረድተዋል።
በሌላ በኩል፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ የአፋር ተወላጆች፣ ለፋኖ ወታደራዊ መረጃ ታቀብላላችሁ ተብለው ከታሰሩ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ጋር፣ በአፋር ክልል ልዩ ስሙ መጋሊ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ ድብቅ እስር ቤት እና በአዋሽ አርባ፣ አንድ ላይ ታስረው እንደሚገኙ ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በሌላ መረጃ፣ ከዚህ ቀደም በፌዴራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ተደርጎ በነበረው ጦርነት ወቅት የታሰሩ የህወሓት የጦር መሪዎች፣ ዛሬም ድረስ በአሶሳ ከተማ አቅራቢያ ታስረው እንደሚገኙ፣ ዞብል ፖስት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ፓዊ አካባቢ ታስረው ስለሚገኙ የአማራ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላትን እስራት ለማጣራት ባደረገው ጥረት መረጃውን ለማግኘት ተችሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ አንዳንድ የህወሓት አዋጊዎች፣ “የፌዴራል መንግስቱ ከህወሓት ጋር ያለው ግንኙነት መልሶ ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል” በሚል ስጋት፣ ከአራት ዓመታት በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ ዞብል ፖስት ከመረጃ ምንጮቹ እግረመንገዱን ሰምቷል።
በተመሳሳይ፣ ከኦነግ እና ኦፌኮ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ፣ የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች፣ በአሶሳ እና በወለጋ አካባቢዎች በሚገኙ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ለመረዳት ችለናል።


