የካቲት 26 2018 ዓ.ም –ዞብል ፖስት ዜና!
የወልቃይት ጠገዴ የማንነት እና የወሰን ጥያቄ አፋጣኝ ሕጋዊ እውቅና እንዲሰጠው በዛሬው ዕለት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄደ ሕዝባዊ ሰልፍ ተጠይቋል።
በሰልፉ ላይ የማንነት ጥያቄን፣ የወሰን መከበርን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ ጠንካራ መልዕክቶችን ተላልፈዋል።
የአማራ ማንነታቸውና የታሪካዊ ወሰናቸው ጉዳይ የማይደራደሩበት ፅኑ አቋማቸው መሆኑን፣ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በዛሬው ዕለት ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ አሳውቋል።
በዛሬው ዕለት በተካሄደው ሰልፍም፣ “አማራነት ፅኑ ማንነታችን እንጅ አወዛጋቢ የፖለቲካ ካርድ አይደለም” የሚለው መፈክር ጎልቶ የተሰማ ሲሆን፣ የወልቃይት ጠገዴ የዘመናት የማንነትና ወሰን ጥያቄ እና እውቅናቸው በሕግ እንዲፀናም ተጠይቋል።
በተለይም “ምዕራብ ትግራይ” የሚለው መጠሪያ የሕወሓት የአፓርታይድ ሥርዓት የጭቆና ምልክት መሆኑን በመግለጽ፣ “ተከዜ ቋሚ ተፈጥሯዊ ወሰናችን ሆኖ ይቀጥላል” ብለዋል።
በሰልፉ ላይ “ሁላችንም የተከዜ ዘቦች ነን” የሚል መሪ ቃል የተሰማ ሲሆን፣ ሕዝቡ ለአማራዊ ማንነቱና ለወሰኑ የተከዜ ዘብ ነው የሚል የትግል መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ህወሓት በወልቃት ሕዝብ የፈፀውን ግፍና የዘር ማጥፋት ወንጀል በማስታወስ ለደረሰባቸው በደል ዛሬም ፍትሕ እንዲሰጣቸው አጥብቀው ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት በአግባቡ እንዲከበር የጠየቁት ሰልፈኞቹ፣ በሀገሪቱ ጦርነት እንዲያበቃና ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎታቸውን ገልጸዋል። እንደ ማንኛውም ዜጋ የመምረጥና የመመረጥ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸውና ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው እንዲረጋገጥ ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ በትግራይ እና በአማራ ክልላዊ መንግሥታት መካከል “አከራካሪ” በተባሉት የሑመራ፣ የአዲረመፅ፣ የኮረም አፍላ፣ የጠለምትና፣ የራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቁጥር ፌደም/አፈ/5/13138 ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ አይዘነጋም።
በዛሬው ዕለት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በተካሄደው ሰልፍ ላይም፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልል ምክር ቤትም ውክልና እንዲሰጣቸው በአፅንኦት ተጠይቋል።


