Saturday, May 23, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችበኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት በማንኛውም ቅፅበት ሊፈነዳ የሚችል "የባሩድ በርሜል...

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት በማንኛውም ቅፅበት ሊፈነዳ የሚችል “የባሩድ በርሜል ሆኗል” ሲል “International Crisis Group” አስጠነቀቀ።

የካቲት 11 2018 ዓ.ም-ዞብል ፖስት ዜና!

ዋነኛ ትኩረቱን በሠላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ አድርጎ የሚሰራው International Crisis Group በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያን እና ኤርትራን እንደዚሁም በትግራይ ክልል ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ አስመልክቶ የጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ዓለም አቀፉ ተቋም ባወጣው አዲስ የጥናት ሪፖርት ላይ እንደተለመላከተው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል እየተባባሰ የመጣው ውጥረት እንደዚሁም በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል መልሶ እያገረሸ ያለው የግጭት አዝማሚያ ወደ ጦርነት ሊቀየር ከጫፍ ላይ ደርሷል ሲል አሳስቧል።

በዐቢይ አህመድ እና በኢሳያስ መንግሥትታት እንደዚሁም በህወሓት መካከል ያለው የተወሳሰበ እና በውጥረት የታጀበውን ግንኙነት “በአፍሪካ ቀንድ በማንኛውም ቅፅበት ሊፈነዳ የሚችል የባሩድ በርሜል” ሲል International Crisis Group የሁኔታውን አሳሳቢነት በሪፖርቱ ገልጾታል።  

ሪፖርቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2018 ዓመተ-ምህረት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ተፈርሞ የነበረው “የአዲስ አበባ-አሥመራ-ባሕር ዳር” ወታደራዊ ጥምረት ሙሉ በሙሉ ፈርሶ፣ አሁን ላይ ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ወደ መጠላላትና ወደ ጦርነት እየተንደረደሩ ነው ሲል ያትታል።

የጥናታዊ ሪፖርቱ ግኝቶች የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃንን ውስጣዊ ክፍፍልና የስጋቱ አንደኛው መነሻ አድርጎ የወሰደ ሲሆን፣ በሕወሓት አመራሮች መካከል ያለውን ስንጥቃት በመጥቀስ በጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ሲሞክር፣ በአንጻሩ በደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ሞንጆሪኖ የሚመራው ሌላኛው የሕወሓት ቡድን ከአሥመራ ጋር የፈጠረው ጥምረት የኢትዮጵያና ኤርትራ ውጥረት አንደኛው መነሻ እንደሆነ ያሳያል።

ይህ በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው የትግራይ ልሂቃን እና ፖለቲከኞች አደገኛ ክፍፍል ትግራይን የኢትዮጵያና የኤርትራ “የውክልና ጦርነት ሜዳ ሊያደርጋት ይችላል” ሲል ዓለምአቀፉ ተቋም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት አስመልክቶ ያለውን ስጋት በሪፖርቱ አብራርቷል።

ሌላኛው የኢትዮጵያ እና ኤርትራን ግንኙነት አስመልክቶ International Crisis Group ልዩ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ከባሕር በር እና የሉዓላዊነት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የወደብ መግባቢያ ስምምነት እና ቀጥሎም የአሰብ ጉዳይ መነሳቱ፣ ኤርትራን ለጦርነት ዝግጁ እንድትሆን አድርጓታል ሲል ይገልፃል።

ሪፖርቱ እንደሚለው፣ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንፃር ሳይሆን የኤርትራን ግዛት ለመቀማት የታለመ “የወረራ ዕቅድ” አድርጎ ነው የሚመለከተው ሲል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በኩል የተነሳውን የባሕር በር ጥያቄ እና የኤርትራን ምላሽ ያትታል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከሩብ ክፍለዘመን በኋላ ወደ ዳግም ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ ሲል International Crisis Group ባወጣው ሰፊ የጥናት ሪፖርት አመላክቷል።

ተቋሙ በጥናት ሪፖርቱ ካካተታቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል ሌላኛው በአማራ ፋኖ እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ሌላኛው ሲሆን፣ ኤርትራ ለፋኖ ታደርጋለች የሚባለውን ወታደራዊ ድጋፍ የዐቢይ አህመድ መንግሥት እንደ ጠብ አጫሪነት እንደሚቆጥረው ተጠቅሷል። ይህ ጉዳይ ሌላኛው ለጦርነት ገፊ ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ፣ ሁለቱ ሀገራት ወደ ግጭት እንዲገቡ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንደኛው መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቅሳል።

ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዎችም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጦርነት እንዲቀሰቀስ ሊያደርጉ የሚችሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ልዩ ትኩረት የሰጠው ሪፖርቱ፣ በሱዳን ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት ለኢትዮጵያና ኤርትራ የጦር መሣሪያ ዝውውርና የታጣቂዎች መሸሸጊያ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር፣ በሱዳን ያለው ቀውስ የሁለቱ ሀገራት ውጥረት ሲታከልበት ከቀይ ባሕር እስከ ናይል ተፋሰስ ድረስ ያለውን ሠላም አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ቀጠና ላይ ያንዣበበውን ስጋት አክሎ ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት አረብ ኢመራቶች ለኢትዮጵያ የምታደርገው የድሮንና የገንዘብ ድጋፍ፣ እንዲሁም ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ ለኤርትራ ያላቸው ቅርበት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት ወደ ግጭት የሚያመራ ከሆነ፣ ጦርነቱ በአፍሪካውያን ብቻ የማይወሰን እና ዓለም አቀፋዊ መልክ እንዲኖረው የሚያደርግ ይሆናል ሲል የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በኢትዮጵያና ኤርትራ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት አንድምታ አያይዞ ገልጿል።

የአፍሪካ ሕብረትና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ግጭቱን የመቆጣጠር አቅማቸው እጅግ መዳከሙን በመጠቆም የአህጉራዊ እና ቀጠናዊ ተቋማት ድክመት ጦርነትን ለማስቀረት የሚቻልበትን ዕድል ጠባብ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሷል። 

በኢትዮጵያና ኤርትራ እንደዚሁም በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ልዩ ትከሩት ሰጥቶ ሰፋ ያለ የጥናት ሪፖርት ይፋ ያደረገው International Crisis Group ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም አሜሪካና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት በአስቸኳይ ጣልቃ ገብተው አዲስ አበባና አሥመራን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ካላመጡ፣ የፈረንጆቹ 2026 ዓመተ ምህረት የአፍሪካ ቀንድ ወደማይወጣበት ቀውስ ውስጥ ይገባል ሲል ምክረ ሃሳቡን አስቀምጧል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ተቋሙ “አፍሪካ በዚህ ዓመት ልዩ ትኩረት ልትሰጣቸው የሚገቡ 7 የሠላምና ፀጥታ አሳሳቢ ጉዳዮች” በሚል በፈረንጆቹ የካቲት 9 2026 ዓመተ-ምህረት ይዞት በወጣው ሌላኛው ሪፖርቱ ላይ የኢትዮጵያና ኤርትራን ውጥረት ማካተቱ አይዘነጋም። 

ተቋሙ ይህንን ስጋቱን እየገለፀ በሚገኝበት ሰዓት ግን፣ ሁለቱ ሀገራት የሜካናይዝድ ጦራቸውን እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው እግረኛ ሠራዊታቸውን ወደሚዋሰኑባቸው የድንበር አቅራቢዎች እያስጠጉ፣ እንደዚሁም የሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላን መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን እየተከሉ እንደሚገኙ ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው በመውጣት ላይ የሚገኙ የተለያዩ ተጨባጭ መረጃዎች ያሳያሉ።

ተቋሙ በዚሁ አዲስ ሪፖርቱ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ቢቀሰቀስ ቀደም ሲል ከነበረው እና ከግጭት ገና ባላገገሙ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ እጅግ የከፋ ሰቆቃ እና ሰብአዊ ቀውስ እንደሚያስከተል አፅንኦት ሰጥቶ አሳስቧል።

ይህ ስጋት በጦር ሜዳ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር የጀመረችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም አደጋ ላይ የሚጥልና የውጭ ድጋፎች እንዲቋረጡ በማድረግ፣ በዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ አሁን ካለው አስከፊ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የከፋ ውጤት የሚያስከትል መሆኑን International Crisis Group በሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አስረድቷል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች