ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በትናንትናው ዕለት ባወጣው የ2024 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት ላይ ይፋዊ ምላሽ ሰጥቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብትና የሠራተኛ ጉዳዮች ቢሮ፣ በፈረንጆቹ 2024 የነበረውን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች የሚመለከተውን ሪፖርት እና ተያይዞ የቀረበውን ግምገማ አፋሕድ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ በበጎ እንደሚመለከተው በመግለጽ ለሪፖርቱ ይፋዊ ምላሽ ሰጥቷል።
ድርጅቱ የሪፖርቱን ሚዛናዊ አቀራረብና ከታማኝ ምንጮች መረጃ የማሰባሰብ ጥረትን እውቅና በመስጠት፣ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ምላሽ የሚሰጠው ገንቢ በሆነ ትብብርና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ከአሜሪካ መንግሥት በሚጋራው መርህ ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ ገልጿል።
አሜሪካ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለዲሞክራሲያዊ እሴቶችና የሰው ልጅ ክብር ከፍተኛ ቦታ የምትሰጥ ሀገር እንደመሆኗ፣ በኢትዮጵያ ውስብስብና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ላይ ቀጣይነት ያለው ትኩረት መስጠቷ አበረታች እርምጃ መሆኑን በመጥቀስ፣ አፋሕድ በሪፖርቱ ላይ በተካተቱ ይዘቶች ዙሪያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱን እና አጠቃላይ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ታሳቢ ያደረገ ምላሽ ሰጥቷል።
በዚህም የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ምላሽ ከሰጠባቸው ጉዳይ መካከል አንደኛው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በሪፖርቱ ላይ ፋኖን “ሚሊሻ” ብሎ መግለፅ ተገቢ አለመሆኑን የሚጠቁመው ክፍል ሲሆን፣ አገላለፁ የፋኖን ትክክለኛ ባህሪና መዋቅር የሚገልፅ እንዳልሆነና ሚሊሻ የሚለው አገላለጽ በኢትዮጵያ አውድ በመንግሥት የሚደራጁና የሚታጠቁ አካላት ሲሆኑ፣ ፋኖ ግን በታሪክና በባህል የአማራ ሕዝብ ማንነት ላይ የተመሰረተ፣ ከመንግሥት ውጭ የሆነ፣ በማኅበረሰብ ላይ የተመሰረተና ራሱን ያደራጀ እንቅስቃሴ ነው ሲል በመግለጫው አትቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በትናንትናው ዕለት ባወጣው ሪፖርት በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) እና በአማራ ፋኖ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ሰፊ ሕገወጥ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያመላክቱ ሪፖርቶች አሉ ብሏል።
አፋሕድ በበኩሉ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸምን ማንኛውንም ሕገወጥ ግድያ እንደሚያወግዝ በመግለፅ፣ የአሜሪካ መንግሥት ስማቸው ከፋኖ ጋር የሚያያዝ ሌሎች አደረጃጀቶች እንዳሉ እንዲረዳ እና በመሰል ሪፖርቶች ላይ ሁሉንም አደረጃጀቶች በአንድ የወል ስም መጥቀስ ተገቢ አይደለም በማለትተጠያቂነትን በሚመለከት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ነጥሎ መጥቀስ ይገባል ሲጥሪ አቅርቧል።
ድርጅቱ ከዚህም በተጨማሪ “ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን ለማክበር ያለንን ቁርጠኝነት የምናረጋግጥ ሲሆን፣ በገለልተኛ ወገኖች ለሚደረጉ ምርመራዎች ትብብር ለማድረግ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነን” ብሏል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሪፖርት ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን (OHCHR) መሠረት፣ ከፈረንጆቹ ጥር 2023 እስከ ጥር 2024 ድረስ በሀገሪቱ ውስጥ ቢያንስ 1,351 ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 741 በአማራ ክልል ውስጥ መሆኑን የሚጠቁመው ክፍል አንዱ ነው።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት በበኩሉ፣ የተጠቀሰው ቁጥር በአማራ ክልል ያለውን ጦርነት ተከትሎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመው ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባወጣው ሪፖርት ላይ የሟቾችን ቁጥር በእጅጉ አሳንሶ ማቅረቡን አሳውቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ እና ገለልተኛ ታዛቢዎች የመንግሥት ወታደራዊ ዘመቻውችና በአየር ጥቃቶች በተፈፀሙባቸው ቦታዎች እና ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ላይ ከተጠቀሰው ቁጥር እጅግ የላቀ የሞት መጠን ይፋ ማድረጋቸውን አፅንኦት ሰጥቶ ገልጿል።
አፋሕድ በመግለጫው ላይ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ሌላኛው “ምዕራብ ትግራይ” የሚለውን የቃል አጠቃቀም ሲሆን፣ ስያሜዊ የታሪክ ሕጋዊነት የሌለው፣ በኃይልና ሕገ-መንግሥታዊ ሂደቶችን ባልተከተለ መንገድ የተመሰረተ ሕገወጥ የግዛት ስያሜ መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱን አገላለጽ ኮንኗል።
በተጨማሪም “ምዕራብ ትግራይ” የሚለው ስያሜ ህወሓት ወደ ስልጣን በመጣበት በ1983 ዓ.ም ወቅት በታሪክ የአማራ ሕዝብ አስተዳደር ሥር የነበሩትን የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎችን በግድ ወደ ትግራይ ክልል ካካለሉ በኋላ የተጀመረ ነው ብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ በግንቦት 16 ቀን 1979 በአሜሪካ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቤተ መጻሕፍት የታተመን ሰነድ በማስታወስ፣ በታሪክ “ምዕራብ ትግራይ” ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ ሽሬ እንጂ ወልቃይትና ጠገዴ አለመሆኑን ሰነዱ በግልፅ እንደሚያሳይ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት በመግለጫው ላይ ትኩረት ሰጥቶ ገልጿል።
በዚህም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትና አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ፣ “ምዕራብ ትግራይ” የሚለውን ቃል በይፋዊ መግለጫዎች ላይ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፤ የአካባቢውን ሕዝብ ማንነትና ቅርስ በትክክል የሚያንጸባርቁ እንደ “ወልቃይት–ጠገዴ–ሰቲት–ሑመራ” እና “ራያ” የሚሉትን ትክክለኛና ታሪካዊ መሠረት ያላቸው ቃላትን መጠቀም፤ ታሪካዊ ሰነዶችንና የሕዝብ ቁጥር መረጃዎችን መሠረት አድርጎ የአስተዳደር ጥያቄዎችን የሚያጣራ ገለልተኛና ግልጽ የአስተዳደር ወሰን ኮሚሽን እንዲቋቋም ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው አፋሕድ ጠይቋል።
አፋሕድ መግለጫውን ሲያጠቃልል የዓለም አቀፍ ክትትልና ተደራሽነትን የተመለከተ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ እንዲረጋገጥ እንደሁልጊዜው የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አሳውቋል።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮችን አንድ አድርጎ ከመመልከት መቆጠብ እንደሚያስፈልግ፣ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ገለልተኛና የማያዳላ ምርመራ እንዲደረግ ድጋፍ ማድረግ፤ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች፣ እና የሰብዓዊ መብት ታዛቢዎች በግጭት ወደተጎዱ አካባቢዎች ያለምንም ገደብ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ፣ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ከሁሉም ታማኝ ዓለም አቀፍ አካላት ጋር ለመተባበር ዝግጁ ነን ሲል ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል።


