ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም ዞብል ፖስት ዜና!
የሱዳን ብሔራዊ ጦር ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው በፈፀሙት ጥቃት የእርሻ ጣቢያዎችን ማቃጠላቸውን እና ንፁሐንን መግደላቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ወታደሮቹ 22 የእርሻ ጣቢያዎችን በተለያዩ ቦታዎች ያቃጠሉ ሲሆን፣ በጥቃቱ ንፁሐንን መግደላቸና እና አፍነው መውሰዳቸው ተነግሯል።
የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በርካታ የእርሻ ቦታዎችን ባቃጠሉበት ጥቃት ወታደሮቹ አራት ሰዎችን መግደላቸውን የመረጃ ምንጫችን አያይዘው የገለጹ ሲሆን፣ የሟቾቹን አስከሬን አንሰጥም ማለታቸውም ታውቋል።
ወታደሮቹ ጥቃት ካደረሱባቸው ቦታዎች መካከል በቃፍቲያ ሁመራ ወራዳ ልዩ ቦታው ሉግዲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሦስት የእርሻ ጣቢያዎችን አቃጥለዋል ተብሏል።
በቃፍቲያ ሁመራ ከተፈፀመው ጥቃት በተመሳሳይ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳም ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን፣ በዚሁ አካባቢም ሌሎች ሦስት የእርሻ ጣቢያዎችን ማቃጠላቸውን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
የሱዳን ጦር ወታደሮች ከፍተኛ ውድመት ያደረሱት በመተማ ፎርገና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፈፀሙት ጥቃት ሲሆን፣ በጥቃቱ 16 የእርሻ ጣቢያዎች መውደማቸውን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በጥቃቱ የተገደሉት አራቱ ንፁሐን በመተማ አደም ግሪን ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሲሆን፣ በጥቃቱ የተገደሉትን ንፁሐን አስከሬን አይነሳም ብለው መከልከላቸውን ጉዳዩን በዝርዝር ያስረዱት የዞብል ፖስት ምንጮች ገልጸዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመው ነሐሴ 5 ቀን ሲሆን፣ በተለይ በመተማ ፎርገና በኩል በተፈፀመው ጥቃት የሱዳን ወታደሮች የቡድን መሳሪያ ጭምር በመጠቀም በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸው ተነግሯል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሱዳን ጦር ወደ ድንበር አዲስ ኃይል እያስጠጋ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን፣ ሉግዲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሱዳን ጦር እና የህወሓት ታጣቂዎች በጥምረት ፈፅመውታል በተባለ ጥቃት በአካባቢው በሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሁለት ባለሀብቶችን አግተው መውሰዳቸው ተነግሯል።
የሱዳን ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ጥቃት ሲፈፅሙ ይህ ሁለተኛው ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በፊት በምዕራብ አርማጭሆ ደለሎና ስናር በሚገኙ ሁለት መንደሮች ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች ሁለት በግብርና ስራ የተሰማሩ ዜጎችን ገድለው፣ አራት ያህሉን አቁስለው፣ ስድስት የሚሆኑትን ደግሞ አፍነው መውሰዳቸውን እና እና ከመቶ በላይ የሚሆኑ የቁም ከብቶችን ዘርፈው መውሰዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።


