ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የሱዳን ጦር ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ጥቃት መፈፀማቸው ተነግሯል። የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የገቡት የሱዳን ወታደሮች ጥቃት ያደረሱት በምዕራብ ጎንደር ምዕራብ አርማጭሆ በሚገኙ መንደሮች ላይ ሲሆን በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ድንበር አቋርጠው ጥቃት ያደረሱት ወታደሮች በጄኔራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ጦር ወታደሮች ሲሆኑ፣ ባሳለፍነው ሠኞ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በመግባት ሠላም በር እና አቦጢር በተባሉ ቦታዎች ላይ ላይ ድንገተኛ ተኩስ መክፈታቸውን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በምዕራብ አርማጭሆ ኢትዮጵያንና ሱዳን በሚያዋስኑት ደለሎና ስናር በሚገኙ ሁለት መንደሮች ላይ በተፈፀመው ጥቃት፣ የሱዳን ወታደሮች ሁለት በግብርና ስራ የተሰማሩ ዜጎችን ገድለው፣ አራት ያህሉን አቁስለው፣ እንዲሁም ስድስት የሚሆኑትን ደግሞ አፍነው መውሰዳቸው ተነግሯል።
ድንበር አቋርጠው ጥቃት የፈፀሙት የሱዳን ወታደሮች በሰው ላይ ካደረሱት ጉዳት በተጨማሪ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የቁም ከብቶችን ዘርፈው የወሰዱ ሲሆን ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችም ከጥቅም ውጭ መደረጋቸውን የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።
የሱዳን ወታደሮች ድንበር ጥሰው ገብተው ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የጦር ሰፈር ሄደው “ልጆቻችንና ከብቶቻችን የተወሰዱት ከኢትዮጵያ ግዛት ነው፣ ከሚደርስብን ጥቃት ጥበቃ አድርጉልን” የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ተገቢውንና አፋጣኝ ምላሽ አላገኘም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጥበቃ አድርጉልን የሚል ጥያቄ ላቀረቡ የአካባቢው ገበሬዎች፣ የሱዳን ጦር ጥቃት ባደረሰባቸው ሁለት መንደሮች አቅራቢያ የሰፈረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አዛዦች “እኛ ከመንግሥት ትዕዛዝ አልተሰጠንም፣ መሰል ችግር ሲፈጠር ዐቢይ አህመድን አናግሩ” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ጉዳዩን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አስረድተዋል።
ባሳለፍነው ወር የሱዳን መገናኛ ብዙሃን “የኢትዮጵያ ታጣቂዎች የአልፋሽጋን መሬት በኃይል ተቆጣጠሩ” የሚል ዜና ማሰራጨታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው መረጃ ግን አካባቢውን የሱዳን ጦር ለአምስት ዓመታት እንደያዘ እና የሱዳን ወታደሮች ወደ ፊት እየገፉ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈፅሙ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያጋሩ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።


