ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት “ድሬዳዋ ከተማ የኦሮሚያ ነበረች” ማለታቸውን ተከትሎ ንግግራቸው በሶማሌ ማኅበረሰብ እና ልሂቃን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን እና ተቃውሞን አስከትሏል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ “ድሬዳዋ ከተማ የኦሮሚያ ነበረች” የሚል ንግግር ያደረጉት ባሳለፍነው ማክሰኞ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር ተከትሎ የሶማሌ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ እና የሚዲያ ባለሙያዎች ቁጣቸውን እየገለፁ እንደሚገኙ በሶማልኛ ቋንቋ ዘገባዎችን ከሚያሰራጩ የሚዲያ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከትናንት በስቲያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ከተሰጡባቸው አጀንዳዎች መካከል አጨቃጫቂ የድንበር እና ወሰን ጉዳዮች አንደኛው ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ድሬዳዋ ከተማ ከኢህአዴግ በፊት የኦሮሚያ አካል ነበረች ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ድሬዳዋ ከተማ ከኢህአዴግ መምጣት በፊት በሕገመንግሥቱ መሠረት የኦሮሚያ አካል ነበረች የሚል ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ “ከኦሮሚያ ተገንጥላ ሄደች” ሲሉ የተደመጠ ሲሆን፣ የተለያዩ የሶማሊኛ ቋንቋ የበይነ መረብ ሚዲያዎች፣ ልሂቃኖች፣ እና ፖለቲከኞች ዋነኛ ትኩረታቸውን በዚሁ ጉዳይ ላይ አድርገው ጠንካራ ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ።
የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር ተከትሎ ድሬዳዋ የኦሮሚያ አካል ለመሆኗ ምንም አይነት የታሪክ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ ዐቢይ አህመድ ጉዳዩን የገለፁበት መንገድ “የግዛት ማስፋፋት እና በኃይል የመዋጥ አካል ነው” ሲሉ የሶማሌ ተወላጆች ጠንካራ ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
በሶማሌ ፖለቲካ ባላቸው ተደማጭነት የሚታወቁትን እና በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች መካከል በድሬዳዋ ላይ በሚነሳው የባለቤትነት ክርክር ዙሪያ በብርቱ ተሟጋችነታቸው ለተደጋጋሚ እስር የተዳረጉትን አደም አላሌን ጨምሮ በርካታ የሶማሌ ልሂቃን በጠቅላይ ሚንስትሩ ሰሞነኛ ንግግር ላይ ጠንካራ ትችት እና ተቃውሞን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
የሶማሌ ተወላጆች በጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ ባነሱት “የግዛት ጥቅለላ” ተቃውሞ ድሬዳዋ ከዚህ ቀደም በየትኛውም ዘመን የኦሮሚያ አካል ሆና እንደማታውቅ እና ከኢህአዴግ በፊትም የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በኢትዮጵያ ክልላዊ አወቃቀር እንዳልነበረ የሚያሳዩ ታሪካዊ ዳራዎችን እየጠቀሱ በመሞገት ላይ ይገኛሉ።
በሶማልኛ ቋንቋ ከሚተላለፉ የሚዲያ አውታሮች የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ድሬዳዋ እና አካባቢው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የኢሳና ጉርጉራ “አውራጃ” በደርግ መንግሥት ጊዜ ደግሞ የኢሳና ጉርጉራ “ራስ ገዝ” ተብሎ ይተዳደር ነበር እንጅ በታሪክ በኦሮሞ አስተዳደር ስር ሆነው አያውቁም በማለት ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና አመራሮች ድሬዳዋ ከተማ እና አካባቢው የኦሮሚያ አካል እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ሲናገሩ የሚደመጥ ሲሆን፣ ይሄንን ተከትሎ በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል የግዛት ይገባኛል ውዝግቦች ምክንያት፣ በከተማዋ እና አካባቢው ባሉ ቀበሌዎች ዛሬም ድረስ የቀጠሉ ውጥረቶች እና ግጭቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል።
ከደርግ ውድቀት ማግስት በተዘረጋው የብሔር ፌደራሊዝም አወቃቀር ምክንያት በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ብርቱ የግዛት ይገባኛል ክርክር የሚነሳባት የድሬዳዋ ከተማ፣ ከአዲስ አበባ በመቀጠል ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥቱ በሆነ የከተማ አስተዳደር ስር በመተዳደር ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል።
የድሬደዋ ከተማ ለበርካታ ዘመናት የተለያዩ ማኅበረሰቦችን በአብሮነት አቅፋ የያዘች እና “የፍቅር ከተማ” ተብላ የምትታወቅ ብትሆንም፣ ከተማዋን ከ1997 ዓ.ም ወዲህ የኦሮሞ እና ሶማሌ ተወላጆች ብቻ እየተፈራረቁ ሲያስተዳድሯት ኖረዋል።
ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድሬዳዋ እና አካባቢው የድንበር ይገባኛል ግጭቶች በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች እየተባባሱ የመጡ ሲሆን፣ የሁለቱ ክልሎች ፀጥታ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ የተኩስ ልውውጥ እስከማድረግ መድረሳቸውን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር ተከትሎ ከሶማሌ ክልል መንግሥት አመራሮችም ሆነ የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ አስተያየት ባይኖርም፣ ጉዳዩ በመንግሥት አመራሮች መካከል ውጥረትን ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ይገመታል።


