ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የሶማሌ የጎሳ መሪዎች ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ “ድሬዳዋ የኦሮሚያ ነበረች” ለሚለው ንግግራቸው ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል ማለታቸውን ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምቷል።
የጎሳ መሪዎቹ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይቅርታ የማይጠይቁ ከሆነ “የሶማሌ ወጣቶች እያስነሱት ያለው ተቃውሞ ተባብሶ ሊደርስ ለሚችለው ጥፋት ተጠያቂ አንሆንም” ሲሉ በዛሬው ዕለት ባካሄዱት ስብሰባ አሳስበዋል ተብሏል።
በዛሬው ዕለት ማለትም ጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በድሬዳዋ ሸረፍ ሆቴል የሶማሌ ተወላጆች ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ የሶማሌ የጎሳ መሪዎች እና ልሂቃን የተገኙ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ላደረጉት ንግግር የሶማሌን ሕዝብ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ባሳለፍነው የሕዝብ ተወካዮች ስብሰባ ወቅት ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል የወሰን ይገባኛል ውዝግቦች ጉዳይ አንደኛው ሲሆን፣ በማብራሪያቸው ላይ “ድሬዳዋ በሕገ መንግስቱ የኦሮሚ ክልል አካል ነበረች” ማለታቸው አይዘነጋም።
ይሄንን ተከትሎ የሶማሌ ልሂቃን እና በሶማሊኛ ቋንቋ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ወዲያውኑ ተቃውሞ ሲያሰሙ መደመጣቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ ከሶማሌ ማኅበረሰብ የተውጣጡ ምሁራን፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እና የጎሳ መሪዎች በድሬዳዋ ከተማ አስቸኳይ ስብሰባን አድርገዋል።
በድሬዳዋ ከተማ ሸረፍ ሆቴል የሶማሌ ጎሳ መሪዎች እና ልሂቃን ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት “ድሬዳዋ የኦሮሚያ አካል ነበረች” በማለት ለተናገሩት ንግግር በይፋ ወጥተው ይቅርታ እንዲጠይቁ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ በሶማሌ ወጣቶቹ ዘንድ እየተነሳ ባለው ተቃውሞ ለሚፈጠር ማናቸውም ችግር የጎሳ መሪዎቹ ሃላፊነት እንደማይወስዱ መግለፃቸውን ለመጽሔታችን የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በአስቸኳይ ስብሰባው ላይ የኢሳ እና ጉርጉራ ዋና የጎሳ መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ የጉርጉራው የጎሳ መሪ ዚያድ ዳውድ ኡመር እና የሰፊው የኢሳ ጎሳ መሪ ሙስጠፌ መሐመድ ኢብራሂምጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሶማሌን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ በመድረኩ ላይ ማሳሰባቸውን የመረጃ ምንጫችን አክለው ገልጸዋል።


