Saturday, May 23, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዜናዋና ዋና ዜናየእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ንግግር እንዲጀምሩ ግፊት ማድረግ ጀምሯል ተባለ።

የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ንግግር እንዲጀምሩ ግፊት ማድረግ ጀምሯል ተባለ።

ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና! 

የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ንግግር እንዲጀምሩ ግፊት ማድረግ መጀመሩን ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው የዲፕሎማቲክ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያሳያል። 

የእንግሊዝ መንግሥት ሁለቱ ሀገራት ወደ ውይይት እንዲገቡ ጫና ማድረግ ጀምሯል የተባለው የኢትዮጵያ መንግሥት እያሳየ ያለውን የወደብ እና የባህር በር ብርቱ ፍላጎት ተከትሎ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እያየለ በመምጣቱ ነው።

የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለዞብል ፖስት ያደረሱት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ሳዑዲ አረቢያ በወቅታዊው የቀይ ባህር አጀንዳ ዙሪያ ሁለቱን ሀገራት እንድታወያይ በእንግሊዝ በኩል ጥሪ ቀርቦላታል ተብሏል።

የእንግሊዝ መንግሥት ሳዑዲ አረቢያ ሁለቱን ሀገራት እንድታቀራርብ ጥሪ ያቀረበው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያን እና ኤርትራን ወደ ሠላም በማምጣት ረገድ የነበራትን ተሞክሮ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለመጽሔታችን አብራርተዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ሁለቱን ሀገራት ለማወያየት ጥረት ማድረግ ጀምሮ እንደነበር ባሳለፍነው ሰኔ ወር መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ሂደቱ እና ውጤቱ ይፋ ባይደረግም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሁለት ጊዜ ውይይት ተደርጎ ያለስምምነት መለያየታቸውን መረጃዎቹ ይጠቁማሉ። 

የእንግሊዝ መንግሥት ሁለቱ ሀገራት ንግግር እንዲጀምሩ ጫና ማድረግ ጀምሯል ከመባሉ ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ አስመልክቶ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ “አሸማግሉን እያልን ነው” ሲሉ መደመጣቸው አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ የባህር በርና ወደብ ፍላጎት ወደጦርነት ሊያመራ እንደሚችል ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሁኔታው ወትሮውንም በጦርነት እና ውጥረት ለሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ሌላ ተጨማሪ ቀጠናዊ ትኩሳትን ይዞ መምጣቱ እየተስተዋለ ይገኛል። 

ይሄንን ተከትሎ ለአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ሲባል ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ንግግር እንዲያደርጉ የእንግሊዝ መንግሥት ጫና በማድረግ ላይ ይገኛል ሲሉ የዞብል ፖስት የዲፕሎማቲክ ምንጮች ከጉዳዩ አሳሳቢነት ጋር አያይዘው አስረድተዋል።

ይሁን እንጅ ለንግግር ጫና በመፍጠር ላይ ነው የተባለው የእንግሊዝ መንግሥትም ሆነ ወደ ንግግር ግቡ የተባሉት የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ አስተያየት አልሰጡም።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር የተገፋችበት መንገድ እና የባህር በር ጥያቄዋ አንገብጋቢነት ብሔራዊ አጀንዳ እየሆነ የመጣ ቢሆንም፣ “ጥያቄው በምን መልኩ ዘላቂ መልስ ያገኛል?” የሚለው ጉዳይ ግን በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን በአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ወገኖች ሲናገሩ ይደመጣል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች