Monday, May 18, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮች"እኔ የኦሮሞ ዋርካ ነኝ" አቶ ሽመልስ አብዲሳ!

“እኔ የኦሮሞ ዋርካ ነኝ” አቶ ሽመልስ አብዲሳ!

ጥቅምት 9/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና! 

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባሳለፍነው ሳምንት የክልሉን ወቅታዊ የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች የሚመለከት ስብሰባ በተደረገበት ወቅት ለጉባኤው ተሳታፊዎች “እኔ የኦሮሞ ዋርካ ነኝ” ማለታቸው ተሰምቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይሄንን ያሉት ከኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ እና የክልሉ መንግሥት የተለያዩ አመራሮች ጋር የኦሮሚያ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ ለመገምገም በተካሄደ ስብሰባ ላይ መሆኑን ዞብል ፖስት ከምንጮቹ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

አቶ ሽመልስ የኦሮሞ ዋርካነታቸውን የገለፁት “በእርስዎ የስልጣን ዘመን የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ከፍተኛ መካከፋፈል ውስጥ ገብተዋል፣ የሕዝባችንም አንድነት አደጋ ላይ ወድቋል” የሚል አስተያየት ከተሰብሳቢዎቹ መሰጠቱን ተከትሎ ነው ተብሏል።

እንደ ዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች አቶ ሽመልስ አብዲሳ በስብሰባው ላይ “በኦሮሞ ታሪክ እኔ የምመራውን መንግሥት ያህል የኦሮሞን ጠላቶች ያንኮታኮተ፣ ለኦሮሞ ወጣት የስራ ዕድል የፈጠረ፣ የኦሮሞን ባህል ያሳደገ፣ እና ኦሮሚያን በብልፅግና ጎዳና ያስቀመጠ ማንም የለም” ሲሉ ተደምጠዋል።

የክልሉን አጠቃላይ የሠላምና ፀጥታ ጉዳይ አስመልክቶ ጥያቄ እና ትችት የተነሳባቸው አቶ ሽመልስ አብዲሳ “ከላይኛው እስከ ታችኛው ያለው የክልላችን አመራር ከእኔ ጎን ካልቆመ ኦሮሞ በጠላቶቻችን እጅ መልሶ ይወድቃል፣ ከዚህ ቀደም ከደረሰብን የከፋ በደል ይደርስብናል!” ማለታቸውም ተሰምቷል።

በስብሰባው ላይ ለተነሱት ሃሳቦች ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሶማሌ፣ ሲዳማ፣ እና አማራ ክልሎች ጋር ያሉብንን የግዛት ጥያቄዎች ተራ በተራ እየፈታናቸው የማንሄድ ከሆነ ሀምሳ ፐርሰንቱን የኦሮሞ መሬት ልንነጠቅ እንችላለን የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ሃሳብም ሰንዝረዋል ተብሏል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን በድርድር እና በእርቅ በቁጥር ቀንሰነዋ፣ ለጊዜውም ቢሆን ከእኛ ጋር አንሰራም ያሉትን ቀስ በቀስ ወደ እኛ እናመጣቸዋለን፣ ኦሮሞ ያገኘውን ዕድል በውሉ ያልተረዱት የራሳችን ልሂቃንም ነገ ከነገ ወዲያ ሲገባቸው ከእኛ ጋር መስራታቸው አይቀርም ማለታቸውን መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች