ጥቅምት 6/2018 ዓ.ም-ዞብል ፖስት ዜና!
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር “ከመንግሥት መዋቅር ውጭ የሆነ ታጣቂ ቡድን እያደራጁ ነው” የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ዞብል ፖስት ከድሬዳዋና አካባቢው ምንጮች ያገኘው መረጃ ያሳያል።
ከንቲባው ክስ የቀረበባቸው በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አደም ፋራህ እና በገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ መሆኑን መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።
እንደ ዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች ከንቲባ ከድር ጁሃር ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ መዋቅር ውጭ ያደራጁት ታጣቂ ቡድን “በድሬዳዋ ከተማ ዙሪያ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች በሚፈጠሩ የፀጥታ መደፍረሶች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ነው” የሚል ክስ ከአቶ አደም ፋራህ እና አቶ አህመድ ሽዴ ቀርቦባቸዋል ተብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በጅቡቲ መውጫ እንዲሁም በድሬዳዋ ዙሪያ ባሉ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አቶ ከድር ጁሃር አደራጅተውታል ከተባለው ታጣቂ ቡድን ጋር ባሳለፍነው ሳምንት የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ይሄንን ተከትሎ በድሬዳዋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ አካባቢዎች ሲከሰቱ የነበሩ የፀጥታ መደፍረሶችን “በኦነግ ሸኔ ማሳበቡ መቆም አለበት” የሚል ጠንካራ ወቀሳ ከሶማሌ ተወላጆች እንደሚደመጥ የመረጃ ምንጫችን ከጉዳዩ ጋር አገናኝተው አስረድተዋል።
አቶ አደም ፋራህ እና አቶ አህመድ ሽዴ በድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ላይ ከመንግሥት መዋቅር ውጭ የሆነ ታጣቂ ቡድን አደራጅተዋል የሚል ክስ ከማቅረብም በተጨማሪ፣ በአካባቢው የፀጥታ ችግር እንዲከሰት እያደረጉ ካለው ተሳትፎ እንዲታቀቡ ማስጠንቀቂያ ያዘለ መልዕክት መላካቸው ተነግሯል።
በኦሮሞ እና ሶማሌ ክልሎች መካከል በተለያዩ ጊዜያት በድሬዳዋ ከተማ ላይ የይገባኛል ውዝግቦች እና ግጭቶች ሲከሰቱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ከሰሞኑ በከተማዋ ከንቲባ እና በሁለቱ የሶማሌ ተወላጅ ባለሥልጣናት መካከል የተሰማውን መቃቃር ተከትሎ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ይታይ የነበረው አለመረጋጋት መልሶ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋትን አጭሯል።
ዞብል ፖስት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ለቀረበባቸው ክስ ምላሻቸውን ለመስማትና በዚህ ዜና ለማካተት አቶ ከድር ጁሃርን ለማናገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።


