ሰኔ 2/2017 ዓ.ም – ዞብል ፖስት ዜና
በአፋር ክልል ወታደራዊ ስልጠና የጀመረውን የህወሓት ተገንጣይ ክንፍ፣ ከህወሓት የወጡ ከፍተኛ ጄኔራሎች በስፍራው ተገኝተው መጎብኘታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልፀዋል።
የህወሓትን ለሁለት መሰንጠቅ ተከትሎ ከእነ ደብረፅዮን የተገነጠለው እና በጌታቸው ረዳ ይመራል የተባለው ቡድን፣ በአፋር ክልል ሰራዊት ማደራጀት እና ወታደራዊ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ዞብል ፖስት ቀደም ብሎ መዘገቡ ይታወሳል። ከሰሞኑ ደግሞ ከህወሓት የወጡ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ቡድኑ ስልጠና በሚወስድበት የአፋር ክልል ተገኝተው መጎብኘታቸው ተሰምቷል።
በአፋር ክልል በሚገኝ ነፃ መሬት ወታደራዊ ስልጠና የጀመረውን የህወሓት ተገንጣይ ክንፍ በስፍራው ተገኝተው ከጎበኙት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች መካከል፣ ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ እና ጄኔራል ንጉሥ አበጄ (ወዲ ራያ) እንደሚገኙበት ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
ከዚህ ቀደም በአፋር ክልል የትጥቅ ትግል ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል የተባለውን የህወሓት ተገንጣይ ቡድን፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል ተብሎ ተዘግቦ ነበር። ይሁንና፣ “እኔ በትግራይ የእርስ በርስ መጠፋፋትን አልደግፍም ቡድኑንም አልጎበኘሁም” በማለት ጄኔራል ሳሞራ ማስተባበላቸው ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ በአፋር ክልል ተገኝተው ወታደራዊ ስልጠና የጀመረውን ቡድን ከጎበኙ በኋላ፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራውን ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲን ቢሮ በአዲስ አበባ ተገኝተው መጎብኘታቸውን እና በፓርቲው ስብሰባ ላይ መሳተፋቸውን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በሌላ በኩል በደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት መጀመሩ እና “ፅምዶ” የተሰኘ የኤርትራንና የህወሓትን ወታደራዊና ፖለቲካዊ መሪዎችን፣ እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎችን የያዘ ጥምረት መፈጠሩን መረጃዎች ያሳያሉ።
በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ በተፈጠረው የልሂቃን ክፍፍል ምክንያት፣ ከህወሓት የወጡ የቀድሞ ታጣቂዎች፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎች፣ እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች ለሁለት ጎራ ተከፍለው የሚያደርጉት ፍትጊያ “ወደ የት ሊያመራ ይችላል?” የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል።