Wednesday, May 6, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዜናዜና ትንታኔብርጌድ ንሓመዱ የተሰኘው የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና መጀመሩ ታወቀ 

ብርጌድ ንሓመዱ የተሰኘው የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና መጀመሩ ታወቀ 

የኤርትራው የተቃዋሚ እንቅስቃሴ ብርጌድ ንሓመዱ፣ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ አባላቶቹ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት መጀመሩ ተሰምቷል። እንቅስቃሴውን የሚመሩት ግለሰቦች በአዲስአበባ ፅህፈት ቤት መክፈታቸው የተሰማው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር።

በዐቢይ አህመድ መንግሥት እንደሚደገፍ የሚነገርለት ይህ ቡድን፣ በየካቲት፣ 2017 ዓ.ም በአዲስአበባ የከፈተውን ቢሮ “ለወታደራዊ ማዕከላዊ ፅህፈት ቤትነት የመጠቀም ዕቅድ እንዳለው” ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ለቢቢሲ አማርኛ ገልፆ ነበር።

ብርጌድ ንሓመዱ በቅርቡ በኢትዮጵያ በሁለት ቦታዎች ወታደራዊ ስልጠና መጀመሩን ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ወገኖች ሰምቷል። ቡድኑ ወታደራዊ ስልጠና የጀመረበት አንደኛው ቦታ፣ በአፋር ክልል የሚገኘው ልዩ ስሙ “መጋሊ” የተባለ ስፍራ ሲሆን፣ ሌላኛው ወታደራዊ ማሰልጠኛ ቦታ ግን ሚስጥራዊ እንዲሆን መደረጉ ተሰምቷል።

ብርጌድ ንሓመዱ ወታደራዊ ስልጠና ማድረግ ጀምሮበታል በተባለው የአፋር ክልል፣ ከአዲስአበባው ቢሮ ቀጥሎ ሌላ ቢሮ የመክፈት እቅድ እንደነበረው የንቅናቄው አመራሮች ከአንድ ወር ገደማ በፊት ከቢቢሲ አማርኛ ዜና ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልፀው ነበር።

የብርጌድ ንሓመዱን እንቅስቃሴ ከፊት ሆነው ይመሩታል ከሚባሉት አንዱ የሆኑት የዲፕሎማሲ ክንፍ ሃላፊው አቶ በየነ ገብረእግዚአብሔር፣ “የኢሳያስ አፈወርቂን መንግሥት ለመጣል ለሚያደርጉት ትግል የኢትዮጵያ መንግሥት የድርሻውን የሚወጣ ከሆነ፣ የኢትዮጵያን የባህር በር እና ተያያዥ ጥያቄዎችን እኛ ልንመልስላቸው እንችላለን” በማለት ለቢቢሲ የአማርኛው ዜና ክፍል ባለፈው ሚያዚያ ወር ገልፀው ነበር።   

በ2010 ዓ.ም ወደ ሠላማዊ ግንኙነት ተቀይሮ የነበረው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት፣ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመውን የፕሪቶሪያው ስምምነት ተከትሎ መልሶ መሻከሩ ይታወሳል። ይህ ሂደት፣ ብርጌድ ንሓመዱ የተባለው ንቅናቄ የኤርትራን መንግሥት ለመጣል ጀምሬያለሁ ያለውን ትግል በኢትዮጵያ እንዲጀመር ዕድል ሊፈጥርለት እንደቻለ ይገመታል።

ብርጌድ ንሓመዱ ወታደራዊ ስልጠና ያደርግበታል በተባለው በአፋር ክልል በሚገኘው የመጋሊ ቀጠና፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ከፍተኛ መከፋፈል ምክንያት፣ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ይሰራሉ ተብለው የሚታሰቡ ከህወሓት የወጡ ታጣቂዎች እና ወታደራዊ መሪዎች ጭምር ወታደራዊ ስልጠና የሚያካሂዱበት አካባቢ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ኤርትራን ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ እያስተዳደሩ የሚገኙት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የኤርትራ 34ኛ ዓመት የነፃነት በዓል በሚከበርበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ “ዐቢይ አህመድ በኤርትራ ላይ ለሚያስቡት ሴራ የአፋርን መሬት ይጠቀማሉ” በማለት ክስ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በውጥረት እና አንዱ የሌላኛውን የተቃዋሚ ኃይል በመደገፍ ይታወቅ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት፣ በ2010 ዓ.ም ማብቂያ ያገኘ መስሎ ነበር። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታዩ ባሉ ለውጦች ምክንያት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ፍጥጫ እና ዲፕሎማሲያዊ መካረር መልሶ ሊነግስ እንደሚችል የብዙዎች ግምት ሆኗል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች