Saturday, May 2, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዜናዜና ትንታኔሱዳን ወደ ሁለት ሀገራት የመከፈል ስጋት እያየለባት መምጣቱ ተነገረ

ሱዳን ወደ ሁለት ሀገራት የመከፈል ስጋት እያየለባት መምጣቱ ተነገረ

ሁለት ዓመታትን በደፈነው የሱዳኑ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት፣ የብሔራዊ ጦር መሪ በሆነው ጄኔራል አልቡርሃን በኩል ሳዑዲ አረቢያ እና ግብፅ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ በሆነው ሀምዳን ዳጋሎ በኩል ደግሞ የተባበሩት አረብ ኢሜሬት ተሰልፈው በሚያደርጉት ፍልሚያ፤ ሱዳን ወደ ሁለት ሀገራት የመሰንጠቅ ስጋት ውስጥ አስገብተዋታል ተብሏል።

በጦርነቱ የኃይል ሚዛን በየጊዜው ተቀያያሪ አሰላለፍ በጉልህ የሚታይበትን የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጣልቃገብነት እያስተናገደ ባለው የሱዳን ቀውስ፣ የጦር መሳሪያ መተላለፊያ መስመር በመሆን፣ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማቅረብ፣ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን በመላክ፣ እንዲሁም በጦርነቱ ላይ የመረጃ ድጋፍ በማድረግ፣ የተለያዩ ሀገራት ሱዳንን በጥምር እያፈረሷት ይገኛሉ።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሚያዝያ 15፣ 2025 “የሰላምና አንድነት መንግሥት” የተባለ ትይዩ መንግሥት ማቋቋሙን አሳውቋል። የፈጥኖ ደረሹ ኃይል ዋና አዛዥ የሆኑት ጀኔራል ሞሐመድ ዳጋሎ፣ “ለአዲሲቷ ሱዳን መሠረት የሚጥል የሽግግር ሕገ-መንግሥት አፅድቀናል” ያሉ ሲሆን፣ ይህ ሂደት ግን ሱዳንን ለሁለት የሚከፍል ምዕራፍ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትን ጉዳዩን በቅረበት በሚከታተሉ ወገኖች ዘንድ ፈጥሯል፡፡

ከመካከለኛው ምስራቅ በተባበሩት አረብ ኢሜሬት እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት በዐቢይ አህመድ የሚደገፉት ጄኔራል ሀምዳን ዳጋሎ፣ ለሱዳን የሽግግር መንግሥት 15 ተወካዮችን ያቀፈ ፕሬዚዳንታዊ ካውንስል ማቋቋሙን ያወጀው በምዕራባዊ ሱዳን እና በኮርዶፋን ግዛቶች ኃይሉን ካሰማራ በኋላ መሆኑ ተነግሯል። ጀኔራል ዳጋሎ፣ በሀገሪቱ የትኛውም ብሔር፣ ግዛት፣ ወይም ኃይማኖት ከሱዳናዊ ማንነት ሊበልጥ እንደማይገባ የትይዩ መንግሥት ባቋቋሙበት ዕለት ተናግረዋል።

የጦርነቱን ሂደት እየቀለበሰ ካርቱምን ጨምሮ እንደ ኒያላ፣ ዋድ መድኔ፣ እና ኡምዱርማንን ያሉ የሱዳንን አብዛኛውን ግዛቶች መልሶ መቆጣጠር የቻለው በጄኔራል አልቡርሃን የሚመራው የብሔራዊ ጦር፣ የሱዳን መንግሥት ተደርጎ የሚታይ ሲሆን፤ ጦሩ በጀኔራል ዳጋሎ የተመሰረተውን ትይዩ መንግሥት “የክህደት ተግባር” ሲል ገልፆታል፡፡

ከ10 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ያፈናቀለው እና ከ10 ሺ የሚበልጡ ዜጎች እንዲገደሉ ምክንያት ለሆነው ለሱዳኑ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ለሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች ያለው መፍትሔ ሱዳንን ወደሁለት ሀገራት መክፈል የሆነ መስሏል፡፡ ጦርነቱ እልባት እንዲያገኝ በሚል በሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ የተደረጉ የሰላም ጥረቶችም በስኬት ሊጠናቀቁ አልቻሉም።

የቀጠናው ወኪል ድርጅት ተደርጎ የሚታየው ኢጋድ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የሱዳንን ግጭት ለማስቆም አልቻሉም። በአሜሪካ እና ሳዑዲ ጥምረት በሲውዘርላንድ ጄኔቫ እንዲካሄድ ታስቦ የነበረው የድርድር ጥረትም ፍሬ አልባ ሆኖ ቀርቷል፡፡

በነዚህ ምክንያቶች የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ከመቋጨት ይልቅ፣ ሱዳንን ልክ እንደ ሊቢያ ወደ ሁለት በጦርነት የሚቀጥሉ ግዛቶች የመክፈል ዕድሉ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ከዚህ ቀደም የተሞከሩ የሠላም ጥረቶች ሳይሰምሩ መቅረታቸው ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገሮች ከዚህ የከፋ ከሆኑ ደግሞ፣ ሱዳን ልክ እንደ ሱማሊያ የራስ ገዝ መንግሥታትን የሚያውጁ ሃይሎችን ከየአካባቢው ልታዋልድ የምትችልበት ዕድሏ ሰፊ ነው።

በምዕራባዊ ሱዳን በተለይም በዳርፉር ግዛት ሰፊ ወታደራዊ ይዞታ ያለው የጀኔራል ዳጋሎ ጦር፣ አካባቢው ከሊቢያ፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን መሆኑን ተከትሎ፣ ዳርፉር ላይ ራስ ገዝ መንግሥት ሊመስረት ይችላል። ይህ ሁኔታ የሱዳን ጦርነት ከሚፈጠራቸው ቀጠናዊ ስጋቶች አንዱና ዋነኛው ይሆናል፡፡

ከዳርፉር ባሻገር፣ እንደኩርዶፋን እና ብሉናይል ያሉ በሱዳን ማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ በተደጋጋሚ የማመፅ ልምድ ያላቸው ግዛቶች ከመሆናቸው የተነሳ፤ በነዚህ አካባቢዎች ያሉ አማፂያን ዓለማቀፍ ዕውቅና የሌላቸው ራስ-ገዝ አካባቢዎች የመሆን ዕጣ ፋንታ ሊገጥማቸው ይችላል የሚል ስጋትን በቀጠናው ላይ መፍጠራቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች