Monday, June 16, 2025

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዘገባዎችየምርመራ ዘገባበጠለምት የሚንቀሳቀሱ የተራድኦ ድርጅቶች በአካባቢው የሚፈፅሙት ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት እና ለጦርነት ድግሥ የሚጫወቱት...

በጠለምት የሚንቀሳቀሱ የተራድኦ ድርጅቶች በአካባቢው የሚፈፅሙት ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት እና ለጦርነት ድግሥ የሚጫወቱት ሚና!

ሰኔ 9/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት የምርመራ ዘገባ!

ለምርመራ ዘገባው ገፊ ምክንያት 

በግንቦት 28/2017 ዓ.ም፣ የጠለምት አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ “የህወሓት ቡድን ለዳግም ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት አጥብቀን እንቃወማለን፤ ለዘላቂ ሠላም እንታገላለን” በሚል አርዕስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።

በመግለጫው ላይ ከተካተቱት ነጥቦች መካከል በተራ ቁጥር 3 ላይ የሰፈረው “በጠለምት አካባቢ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያድ) በወረቀት የሰፈረውን የምስረታ ዓላማቸውን በሚቃረን መልኩ የፖለቲካ ዓላማ ማራመጃ ሆነዋል” የሚል ሃሳብ ይገኛበታል። መግለጫው አክሎም፣ “መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚፈፅሙት ሴራ እና ሸፍጥ የጠለምት ህዝብ ለዘመናት ያደረገውን የማንነት ትግል እያወሳሰበው ይገኛል” ብሏል።

የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴው፣ “አካባቢው ሰላም እንዳይሆን ችግሩን እያባባሱ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ማሳያ ከተፈለገ፣ የተቋማቱን ስም በዝርዝር እንደምናቀርብ እናሳውቃለን” ማለቱን ተከትሎ፣ ዞብል ፖስት ሁኔታውን በጥልቀት ለመመልከት እና ጉዳዩን የተመለከቱ ግኝቶችን በምርመራ ዘገባ መልክ ለአንባቢያን ለማቅረብ የተለያዩ ወገኖችን ቃለመጠይቅ አድርጓል።  

ይህ የምርመራ ዘገባ በጠለምት አካባቢ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ የተራድኦ ድርጅቶች (NGOs)፣ በተሰጣቸው ሥልጣንና ዓላማ መሠረት እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ እና “ከፖለቲካዊ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር አላቸው ስለተባለው ግንኙነት” በጥልቀት ለመዳሰስ ያለመ ነው።

የምርመራ ዘገባውን ለማጠናቀር በስልክ ላነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረብን ሲሆን፣ በምላሾቻቸው ላይ ተንተርሰን የችግሩን ስፋትና ተፈጥሮ በጥልቀት ለመዳሰስ ችለናል። ይሄንን የምርመራ ዘገባ ለማዘጋጀት ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች ለደህንነታቸው ሲባል ማንነታቸው አልተጠቀሰም። 

በጠለምት አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የተራድኦ ድርጅቶች ማንነትና ህግን ያልተከተሉ ተግባራት

በጠለምት አካባቢ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ከተፈቀደላቸው የሰብዓዊ ድጋፍ እና የልማት ተግባራት ውጭ በፖለቲካዊ ጉዳዮች እየተሳተፉ ነው የሚል ቅሬታ የቀረበባቸው NRC (Norwegian Refugee Council)፣ IOM (International Organizational for Migration)፣ FAO (Food and Agricultural Organization)፣ UNICEF (United Nations Children’s Fund) ፣ WFP (World Food Programme)፣ UNHCR (United Nations High Commissioner for Refugees) ዋነኞቹ እንደሆኑ፣ በቃለመጠይቁ ከተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

እነዚህ ድርጅቶች ከተፈቀደላቸው የሰብዓዊ አገልግሎት እና የልማት ስራዎች ውጭ ህግን ያልተከተሉ በርካታ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ፣ ዞብል ፖስት በጉዳዩ ላይ ባደረገው ሰፊ ምርመራ አረጋግጧል።

ዞብል ፖስት የጠለምት እና አካባቢውን በርካታ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ያገኘው ምላሽ እንደሚያመለክተው፣ እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች፣ የአማራ ህዝብ ታሪካዊ የማንነት እና ወሰን ጥያቄዎችን የሚያነሳባቸውን የጠለምት እና ማይጠብሪ አካባቢዎች ወደ ትግራይ እንዲካለሉ፣ ከህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር በአካባቢው ላይ የተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በጥምረት በመስራት ላይ ይገኛሉ።

አንድ በቃለመጠይቁ የተሳተፉ ግለሰብ “የህወሓት አመራሮች በአካባቢው ለሚያደርጉት ፖለቲካዊ ቅስቀሳ አካባቢው ወደ ትግራይ እንዲካለል ህዝቡ ላይ ጫና ማሳደር የሚችሉ የተለያዩ ግለሰቦችን የሚመለምሉ ሲሆን፣ የተራድኦ ድርጅቶቹ በበኩላቸው ለተመለመሉት ሰዎች በነፍስ ወከፍ እስከ 27,000 ብር ይከፍላሉ” በማለት ገልፀዋል።

እኝሁ ግለሰብ አክለውም፣ “የተራድኦ ድርጅቶቹ በጠለምት አካባቢ የሚኖሩ የአገር ሽማግሌዎችን እና የሐይማኖት አባቶችን እየሰበሰቡ የህወሓትን ፍላጎት እንዲቀበሉ እና ህዝቡንም እንዲያግባቡ ጫና ያደርጉባቸዋል” በማለት የተራድኦ ድርጅቶቹን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትና በአካባቢው ላይ እያሳደሩ ያሉትን ፖለቲካዊ ጫና ያስረዳሉ።  

በጠለምትና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ የተራድኦ ድርጅቶች ተሽከርካሪዎች ለህወሓት የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሻ፣ ለፖለቲካዊ ቅስቀሳ፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ ታጣቂዎች በአካባቢው ለሚያደርጉት ቅኝት አገልግሎት እንደሚሰጡ በዚህ የምርመራ ዘገባ ተረጋግጧል።

ለህዝቡ የእርዳታ አቅርቦት በሚከፋፍልበት ወቅት፣ የተራድኦ ድርጅቶቹ ሠራተኞች የድርጅቶቹ መኪኖች ላይ ሆነውና የድምፅ ማጉያ ይዘው የሰብዓዊ ድጋፍ ለማግኘት የተሰበሰበውን ህዝብ “ጠለምት ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም የትግራይ ነው። እናንተም በትግራይ ክልል ውስጥ ነው መኖር የምንፈልገው ማለት አለባችሁ እያሉ ይለፍፋሉ” ሲሉ ሌላኛው ቃለመጠይቅ ያደረግንላቸው ተረጅ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

እነዚህ የተራድኦ ድርጅቶች የእርዳታ ስራቸውን ከማንነት ጥያቄ ጋር በማገናኘት እና ፖለቲካዊ ቅስቀሳዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ፣ “የህወሓትን ፖለቲካዊ ፍላጎት በተረጅዎች ላይ ለመጫን” እየሰሩ እንደሚገኙ በዚህ የምርመራ ዘገባ ለማረጋገጥ ተችሏል። ለመፅሔታችን ሃሳባቸውን ያገሩ አብዛኛዎቹ የቃለመጠይቁ ተሳታፊዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ መልስ ሰጥተዋል።

“የተራድኦ ድርጅቶቹ የስራ ቅጥር ፖሊሲ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ሆኗል!”

በምርመራ ዘገባው ላይ ከተረጋገጡ ጉዳዮች መካከል፣ በፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተግባራት ላይ በሚሳተፉ የተራድኦ ድርጅቶች ውስጥ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በአመራር እና የሙያተኛ የስራ መደቦች ላይ እንዲቀጠሩ ተደርጓል።

በጠለምትና አካባቢው በሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በከፍተኛ ኃላፊነት ከሚሰሩ ግለሰቦች መካከል፣ ነጻነት አደባባይ (NRC)፣ ዓወት (IOM)፣ አባዲ (FAO)፣ ዶ/ር ዮሐንስ (UNICEF)፣ መብራህቶም (UNHCR) እንደሚገኙበት፣ ለመፅሔታችን የደረሰውን መረጃ ተንተርሰን ባደረግነው ሰፋ ያለ የማጣራት ስራ ለማወቅ ችለናል።

በዚህ ዙሪያ ሃሳባቸውን ለመፅሔታችን ያጋሩን የቃለመጠይቁ ተሳታፊ፣ “በእነዚህ የተራድኦ ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊ ተደርገው የተሾሙ እና በሙያተኝነት የሚሰሩ የትግራይ ተወላጆች በድርጅቶቹ እንዲቀጠሩ የተደረገው በተጠና መልኩ ሲሆን፣ ዓላማውም በሰብዓዊ ድጋፍ እና ልማት ስም የጠለምትን ግዛት ወደ ትግራይ ማከለል ነው” በማለት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በአካባቢው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግልፅ ተሳታፊ እንደሆኑ ያስረዳሉ።

በተራድኦ ድርጅቶቹ ውስጥ እንዲቀጥሩ የተደረጉ የትግራይ ተወላጆች ለህዝቡ እርዳታ በሚከፋፍልበት ወቅት ከሰብዓዊ ድጋፍ ውጭ የሆኑ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መልዕቶች እንደሚያስተላልፉ፣ ዞብል ፖስት ካነጋገራቸው ተረጅዎች ለመረዳት ችሏል።

“እርዳታ ለመውሰድ ተሰልፈን በምንጠባበቅበት ወቅት እናንተ አማራ አይደላችሁም ማንነታችሁ ትግራዋይ ነው፣ የሚሉ ፖለቲካ መልዕክቶችን በየጊዜው ይነግሩናል” በማለት መፅሔታችን ያነጋገራቸው አንድ ግለሰብ በተራድኦ ድርጅቶቹ እንዲቀጠሩ የተደረጉ የትግራይ ተወላጆችን ፖለቲካዊ ተልዕኮ ለመፅሔታችን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ዞብል ፖስት ከአካባቢው ነዋሪዎች የቀረቡለትን አንዳንድ ሰነዶችን አገላብጦ ከተመለከተ በኋላ፣ አብዛኛዎቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች “Tigray Response” በሚል የትግበራ እንደሚንቀሳቀሱ ለማወቅ ችለናል። “እቅዱ የጠለምትን አካባቢ ወደ ትግራይ የማካለል ፕሮጀክት አካል ነው” በማለት ሰነዱን ያሳዩን የአካባቢው ነዋሪዎች አያይዘው ይገልፃሉ።

የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት

የህወሓት የፖለቲካ አመራሮች እና ወታደራዊ አዛዦች በጠለምት አካባቢ በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ተጠቅመው በአካባቢው ላይ ያላቸውን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ፍላጎት ለማሳካት እንደሚንቀሳቀሱ፣ ቃለመጠይቅ ያደረግንላቸው ግለሰቦች የሰጡት ምላሽ ያመላክታል።

የህወሓት ወታደራዊ አመራሮች በጠለምት አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅግ የጠበቀ ሲሆን፣ ከተራድኦ ድርጅቶፉ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር በየጊዜው እንደሚገናኙ ለዞብል ፖስት ከተሰጡት ምላሾች መረዳት ችለናል።

እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የህወሓትን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈፀም እንደ መሳሪያ ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፣ የህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በአካባቢው ያላቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚያስፈፅሙ ወጣቶችን በመልመል ሲያሰማሩ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ ለዚሁ ተግባር የሚያስፈልገውን የገንዘብ እና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን በማቅረብ እንደሚተባበሩ ለማወቅ ተችሏል።

አንድ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ ስለሁኔታው ሲያስረዱ፣ “የህወሓት ታጣቂዎች በሌሊት ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ፣ የጠለምት ህዝብ የትግራይ አካል ነው። አማራ ነኝ የሚል ካለ በህይወቱ እንደፈረደ ይቁጥረው በማለት የአማራ ተወላጆችን በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ” በማለት የሚደርስባቸውን እንግልት ያስረዳሉ። አክለውም፣ ስርቆት፣ ግድያ፣ የሰው እገታ፣ እና የመንገድ ላይ ዝርፊያ በየጊዜው እየተፈፀመ እንደሆነ እና የህዝቡ ደህንነት አደጋ ላይ እንደወደቀ ገልጸዋል።

አንድ የጠለምት አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አመራር የሆኑ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ በበኩላቸው፣ በአካባቢያችን የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች “የጠለምት አማራ ማንነት ጥያቄን ለማኮላሸት እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች “እኔ ትግራዋይ ነኝ” እንዲሉ በማስገደድ የሰብዓዊ እርዳታን ለፖለቲካዊ መሳሪያ እየተጠቀሙበት ይገኛል” በማለት ሁኔታውን ያብራራሉ።

አክለውም፣ “በጠለምት እና አካባቢው የተሰማሩ የተራድኦ ድርጅቶች፣ የሰብዓዊ ድጋፍን እንደሽፋን ተጠቅመው በሚፈፅሙት ጣልቃገብነት ሌላ ደም አፋሳሽ ጦርነት በመደገስ ላይ ይገኛሉ” በማለት ሁኔታው ሊያስከትለው የሚችለውን ቀውስ አፅንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ።   

የተራድኦ ድርጅቶቹን ጉዳይ ለማጣራት የአካባቢውን ነዋሪዎች ስናነጋግር፣ በጠለምት የተከዜ ተፋሰስ አካባቢ እንደ ወርቅ፣ እብነበረድ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ኦፓል፣ እና ዕጣን ያሉ ሰፊ መሬት የሚሸፍኑ የተፈጥሮ ማዕድናት እንደሚገኙ በርካታ መረጃዎች መኖራቸውን እግረ መንገዳችንን ለመረዳት ችለናል።

አንድ ጡረታ የወጡ መምህር በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡን አስተያየት፣ “የህወሓት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች እነዚህን ሀብቶች ለመጠቀም የረዥም ጊዜ እቅዳቸው ነው፣ አሁን ላይ ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር አካባቢውን ወደ ትግራይ ለማካለል እየሰሩ ያሉትም ይሄንኑ እቅዳቸውን ታሳቢ በማድረግ ነው” በማለት የጉዳዩን ሌላኛውን ገፅ በማሳየት ለመፅሔታችን አስረድተዋል።

ተረጅነትታችንን እንደ ደካማ ጎን ይጠቀሙበታል

ከተፈጥሮ አደጋዎች እና ጦርነቶች ጋር ተደማምሮ፣ የጠለምት ህዝብ ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ ፈታኝና አሳሳቢ እንደሆነ በዚህ የምርመራ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል። “በአካባቢው ምርታማነት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ በመሆናቸው፣ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ እና የንፁህ መጠጥ ውሃ ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ባለመኖራቸው ህዝቡ ለከፍተኛ ተረጅነት ተጋላጭ ሆኗል” ሲሉ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ የሆኑ ሌላኛው ግለሰብ የአካባቢውን አስከፊ ሁኔታ ያስረዳሉ።

“ከሰብዓዊ ድጋፍ ውጭ የተራድኦ ድርጅቶች በጠለምት ህዝብ ላይ ለሚፈፅሙት ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት ተጋላጭ የሆንንበት ዋነኛው ምክንያት፣ አካባቢው በከፍተኛ ድህነትና ኢኮኖሚያዊ እጦት የተጠቃ በመሆኑና ተረጅነታችንን እንደ ደካማ ጎን በመቁጠራቸው ነው!”። ይህ አቋም ዞብል ፖስት ባደረገው ቃለመጠይቅ የተሳተፉ አብዛኛዎቹ ሰዎች ተመሳሳይ ምላሽ የሰጡበት ዋነኛው ጉዳይ ነው።

በዚህ ቃለመጥይቅ የተሳተፉ አንድ ተረጅ “ማህበረሰቡ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታን የሚፈልግ በመሆኑ፣ የተራድኦ ድርጅቶች በነፍስ ወከፍ በወር 15 ኪሎ ግራም እህል በመስጠት፣ የአካባቢውን ለተረጅነት ተጋላጭ መሆን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ህዝቡን ለማያምንበት የፖለቲካ ዓላማ እየጠመዘዙት ይገኛሉ” በማለት የአካባቢው ህዝብ እንዴት ለተራድኦ ድርጅቶች ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት ተጋላጭነት እንደተዳረገ ይገልፃሉ።

ለጠለምት አካባቢ እና ህዝቡ የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥት የሚሰጡት ትኩረት እጅግ ዝቅተኛ እና ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን፣ “መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምን ይላል?” ብለን ላቀረብንላቸው ተያያዥ ጥያቄ ምላሽ የሰጡን ተሳታፊዎች ሁኔታውን “በቁጭት እና በክህደት ተፈፅሞብናል ስሜት” ይገልፁታል።

“የአካባቢው ህዝብ አመታዊ በጀትም ሆነ ድጎማ ተደርጎለት አያውቅም፤ በዚህ ምክንያት እንደ ጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እና ግብርና ያሉ ለህዝቡ የዕለት ተለት ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ዘርፎች ያለበጀት እንዲንቀሳቀሱ ተደርገዋል፣ ህዝቡም ለተራዘመ ተረጅነት እና በእርዳታ ስም ለሚፈፀሙ ፖለቲካዊ ሴራዎች ተጋላጭ ሆኗል” በማለት አንድ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ ህዝቡ ምን ያክል “ትኩረት እንደተነፈገው” ያስረዳሉ።

ተሳታፊው አያይዘው፣ “ህወሓት በጠለምት ህዝብ ህልውና እና የማንነት ጥያቄዎች ላይ ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ፈተናዎችን እየደቀነ ባለበት ወቅት፣ የፌደራልም ሆነ የአማራ ክልል መንግሥት ለችግሩ ምንም አይነት ተጨባጭ ትኩረት ባለማድረጋቸው፣ የህዝቡን ተረጅነት ለፖለቲካ ዓላማ ለሚጠቀሙ ኃይሎች በእጅ አዙር ተባባሪ ሆነዋል” በማለት ስሜታቸውን አጋርተዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ በፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሰማርተዋል የተባሉት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን አስተያየት በዚህ የምርመራ ዘገባ ለማካተት የተለያዩ ኃላፊዎችን በስልክ እና በኢሜይል ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በአካባቢው የተሰማራው መከላከያ ሠራዊት ሚና

በጠለምት አካባቢ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በመከታተል ረገድ ያለው ሚና እጅግ ደካማና ውጤታማ ያልሆነ እንደሆነ መፅሔታችን ላቀረባቸው ጥያቄዎች ከተሰጡት ምላሾች ለመገንዘብ ችለናል።

በአካባቢው ለተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት በኃላፊነት የተመደቡ አንዳንድ ወታደራዊ አመራሮች፣ ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር ምስጢራዊ የጥቅም ትስስር መዘርጋታቸውን በቃለመጠይቁ ላይ ከተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ምላሽ ለመረዳት ተችሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የቃለመጠይቁ ተሳታፊ፣ “የተራድኦ ድርጅቶቹ በአካባቢው የሚያደርጉትን ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት ለመቃወም ሙከራ ስናደርግ የመከላከያ ሠራዊቱ ወታደሮች በዛቻ እና ማስፈራሪያ ተቃውሟችንን እንድናቆም ያስገድዱናል” በማለት ያስረዳሉ።

ሌላኛው የቃለመጠይቁ ተሳታፊ ደግሞ፣ “የሰብዓዊ እርዳታን ለፖለቲካዊ መሳሪያ ለሚጠቀሙ የተራድኦ ድርጅቶች እና ፖለቲካዊ ቅስቀሳን ለሚያደርጉ የህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በአካባቢው የተሰማሩ የመከላከያ ኃላፊዎች ትብብር ሲያደርጉ መመልከታቸውን፣ ለዚህም ገንዘብ እንደሚከፈላቸው መረጃዎች መኖራቸውን” አያይዘው አስረድተዋል።

የአካባቢው ህዝብ የማንነት እና ወሰን የትግል ዳራዎች እና የተራድኦ ድርጅቶች ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት፣ እንደ መደምደሚያ

የጠለምት ግዛት ምስራቅ ጠለምት፣ ምዕራብ ጠለምት፣ እና ማይፀብሪ ከተማን ያከተተተ ሲሆን፣ ከትግራይ ጋር የሚያዋስናቸው ተፈጥሯዊ ድንበር የተከዜ ወንዝ ነው። አካባቢው እስከ የደርግ መንግሥት የውድቀት ዋዜማ ድረስ በሰሜን አውራጃ ደባርቅ እንዲሁም በጎንደር በጌ-ምድር ክፍለ-ሀገር ስር ይተዳደር የነበረ ነው።

በጠለመት የሚኖረው ህዝብ 86% የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንደሆነ፣ 14% ገደማ የሚሆነው ደግሞ የትግርኛ ቋንቋ እንደሚናገር ታሪካዊ ሰነዶች ያስረዳሉ። ይሁንና ህወሓት በትጥቅ ትግል እየተጠናከረ በመጣበት ጊዜ፣ በደርግ ውድቀት ዋዜማ አካባቢውን ሕገ-መንግስቱ  ከመጽደቁ በፊት ህዝቡ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ውክልናና ተሳትፎ ሳይኖረው በኃይል ወደ ትግራይ እንዲካለል ተደርጓል።

ህወሓትን ከስልጣን ያስወገደው ህዝባዊ ንቅናቄ ከተፋፋመበት ከ2008 ዓ.ም ወቅት አንስቶ፣ የአካባቢው ተወላጆች “የጠለምት አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ” ኮሚቴን በጎንደር ከተማ በማቋቋም፣ ህዝቡ ማንነቱ እና የግዛት ወሰኑ እንዲከበርለት በሠላማዊ መንገድ ሲታገል ቆይቷል።

የፌዴራል መንግሥቱ እና ህወሓት ያደረጉትን ጦርነት ተከትሎ፣ የጠለምት እና አካባቢው ህዝብ ራሱን አደራጅቶ እና መሪዎችን መርጦ በአማራ ክልል ስር ሲተዳደር መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ወዲህ ግን ህወሓት አካባቢውን ወደ ትግራይ መልሶ ለማካለል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።   

በዚህ ሁኔታ፣ በጠለምት አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከተመዘገቡበት ዓላማና የስራ ወሰን ውጪ፣ ግልፅ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ህወሓት አካባቢውን ወደ ትግራይ ለማካለል ለሚያደርገው ጥረት ቀጥተኛ ተባባሪ ሆነው መገኘታቸውን፣ ይህ ዞብል ፖስት በርካታ የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሮ ባጠናቀረው በዚህ የምርመራ ዘገባ አረጋግጧል።

እነዚህ የተራድኦ ድርጅቶች የህወሓትን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም እንደ መሳሪያ እያገለገሉ ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፋቸውንና ሰብአዊ እርዳታቸውን ለፖለቲካዊ ዓላማ እያዋሉት ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ የህወሓትን የፖለቲካ ፍላጎት የሚያስፈፅሙ በርካታ ግለሰቦችን በተለያዩ የኃላፊነት እና የሙያተኛ የስራ መደቦች ላይ በተራድኦ ድርጅቶቹ ውስጥ በተጠና መልኩ እንዲቀጠሩ መደረጉን፣ ዞብል ፖስት ያደረገው ምርመራ አረጋግጧል።

የአካባቢው ህዝብ በከፍተኛ ድህነት እና ኢኮኖሚያዊ መገለል ውስጥ መገኘቱ፣ ለሰብዓዊ ድጋፍ እና ተረጅነት መጋለጡ፣ የፖለቲካ ጣልቃገብነት ለሚፈፅሙ የተራድኦ ድርጅቶች እና በትብብር ለሚሰሩ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች ምቹ ሁኔታን ሊፈጥርላቸው እንደቻለ በዚህ የምርመራ ዘገባ ተመላክቷል።

በበርካታ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ ቀውሶች ውስጥ እያለፈች ባለችው ኢትዮጵያ፣ በጠለምት አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የተራድኦ ድርጅቶች በአካባቢው ላይ የሚፈፅሙት ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት በሀገሪቷ ተጨማሪ “የጦርነት ድግሥ” ሊያስከትል እንደሚችል ዞብል ፖስት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ከተገኙ ምላሾች እና የህዝቡ ስሜቶች ተረድቷል።  

የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥት ለጠለምት አካባቢ የሰጡት ትኩረት እጅግ አናሳ መሆኑ፣ ችግሩ እንዲባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን የምርመራ ዘገባው የተለያዩ የጠለምት አካባቢ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ያገኘው ምላሽ በስፋ ያመላክታል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች