ትናንት ከከሰዓት በኋላ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ታዬ ደንደዓ፣ የዋስትና መብታቸው ተነስቶ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በዛሬው ዕለት ትዕዛዝ መስጠቱ ተሰምቷል።
የቀድሞው የሰላም ሚንስቴር ድኤታ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ፣ ያለ ጠበቃ “በስውር” ወደ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ሲል አዲስ ስታንዳርድ የአቶ ታየን ጠበቃ አነጋግሮ ዘግቧል። በዚህም አቶ ታየ ደንደዓ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱ ተሰምቷል።
የአቶ ታየ ደንደዓ ጠበቃ አያይዘው፣ “እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች የሚከናወኑት በተከሳሹ ጠበቃ በኩል ወይም በፍርድ ቤት በተሰየመ የህዝብ ጠበቃ ፊት ብቻ ቢሆንም፣ ይህ መስፈርት ግን ተጥሷል” ብለዋል። በተጨማሪም፣ “ችሎቱ የተካሄደው በምሳ ዕረፍት በተለምዶ የፍርድ ቤት ሂደቶች የማይካሄድበት ጊዜ ላይ በመሆኑ፣ የአቶ ታየን ዋስትና ለማንሳት በስውር የተዘጋጀ ይመስላል” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፡፡
ከጠበቃው አስተያየት ጋር ተያይዞ፣ አቶ ታየ “ከሀገር ለመውጣት እና በውጭ ሀገር ሆነው ሠላማዊ ትግል ለማቀጠጣል እንቅስቃሴ ጀምረዋል” በሚል በጠቅላይ ሚንስትሩ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን፣ ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ወገኖች አናጋግሮ በትናንትናው ዕለት መዘገቡ ይታወሳል።
አቶ ታየ ደንደዓ ህዳር 23፣ 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በዋስትና እንዲፈቱ መወሰኑን ተከትሎ፣ በህዳር 26፣ 2016 ዓ.ም ከእስር ተፈትተው ጉዳያቸውን በውጭ ሲከታተሉ ነበር።
ይሁን እንጅ አቃቤ ሕግ አቶ ታዬ “ከጠላት ጋር በመተባበር” እና “የፀረ-ሰላም ቡድኖች የሆኑትን ሸኔ እና ፋኖን የሚደግፉ መልዕክቶችን በፌስቡክ ገፃቸው አጋርተዋል” ከሚሉት ሁለቱ ክሶች ነፃ መባል የለባቸውም በሚል ይግባኝ ማለቱን ተከትሎ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአቃቤ ሕግን ይግባኝ በማጽናት, አቶ ታዬ ነፃ ተብለው በነበሩባቸው ሁለቱ ክሶች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።