Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዜናዜና ትንታኔየትግራይ ቤተ-ክህነት በኃይል የተቆጣጠራቸውን አብያተክርስቲያናት ለቅቆ እንዲወጣ ተጠየቀ። 

የትግራይ ቤተ-ክህነት በኃይል የተቆጣጠራቸውን አብያተክርስቲያናት ለቅቆ እንዲወጣ ተጠየቀ። 

የትግራይ ቤተ-ክህነት ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ፣ በህወሓት ታጣቂዎች እገዛ በጉልበት ተቆጣጥሮ ሲያስተዳድራቸው የነበሩትን በራያና አካባቢው የሚገኙ አብያተክርስቲያናትን ለቅቆ እንዲወጣ መጠየቁ ተሰምቷል።

አብያተክርስቲያናቶቹ የሚገኙት በስድስት የራያ ወረዳዎች ሲሆን፣ ከአንድ አመት በፊት የትግራይ ክልል ቤተ-ክህነት፣ “የደቡባዊ ትግራይ ዞን የማይጨው ሀገረ-ስብከት” በሚል፣ በህወሓት ታጣቂዎች እገዛ በኃይል ተቆጣጥሮ ሲያስተዳድራቸው የነበሩ አካባቢዎች ናቸው።

አላማጣ ከተማ፣ ራያ አላማጣ፣ ኮረም ከተማ፣ ራያ ኦፍላ፣ ራያ ዛታ፣ እንዲሁም ጨርጨር የተባሉት ስድስት ወረዳዎች፣ የራያ ሀገረ ስብከት እንደ አዲስ እንዲቋቋምላቸው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ፣ ከግንቦት 6 እስከ ግንቦት 20፣ 2017 ዓ.ም ባካሄደው “አመታዊው ርክበ ካህናት ጉባዔ” ወቅት ውሳኔውን አስተላልፏል።

ውሳኔው እንዳስደሰታቸው የገለፁት አንድ በራያ አላማጣ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ፣ በስድስቱ ወረዳዎች የሚገኙ አብያተክርስቲያናት በኃይል ወደ ትግራይ ቤተክህነት መካተታቸውን ተከትሎ፣ የራያና አካባቢው ምዕመናን የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጉን አስታውሰው፣ ውሳኔውን “ትክክለኛ እና ከአንድ ዓመት በላይ በጉጉት ስንጠብቀው የነበረ” በማለት ለዞብል ፖስት ስሜታቸውን አጋርተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ፣ ከግንቦት 6 እስከ ግንቦት 20፣ 2017 ዓ.ም ያካሄደውን ጉባዔ ተከትሎ የተላለፈውን ውሳኔ በማስመልከት፣ የትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጽ/ቤት መልስ ሰጥቷል። ጽ/ቤቱ ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ የትግራይን ግዛታዊ አንድነትን የሚጥስ ነው!” በማለት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የትግራይ ፀጥታ ኃይል ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት አሳስቧል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የትግራይ ቤተ-ክህነት በሐምሌ 2016 ዓ.ም ለስድስት ኤጲስቆጶሳት በአክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን ሹመት መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በመንበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከፍተኛ ቤተ-ክህነት አማካኝነት፣ በጥቅምት 2017 ዓ.ም “የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ” ብለው ማቋቋማቸው የሚታወስ ነው።

ይሄንን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ “በትግራይ የተደረገው እንቅስቃሴ እና ለትግራይ ኤጲስቆጶሳት ሹመት የተሰጠበት መንገድ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና የሚፃረር ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው” በማለት አውግዛ፣ “አንድ መንበር፣ አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትርያርክ” የሚለው የቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ እና ቀኖና ሊከበር እንደሚገባው በአጽንዖት ማሳሰቧ ይታወሳል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች