Sunday, May 24, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየቱርክ መንግሥት በርካታ የመረጃ እና ደኅንነት ሙያተኞችን በኢትዮጵያ እያሰማራ መሆኑ ተነገረ።

የቱርክ መንግሥት በርካታ የመረጃ እና ደኅንነት ሙያተኞችን በኢትዮጵያ እያሰማራ መሆኑ ተነገረ።

ታሕሣስ 19/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና ትንታኔ!

የቱርክ መንግሥት በርካታ የመረጃ እና ደኅንነት ሙያተኞችን በኢትዮጵያ እያሰማራ መሆኑን ተቀማጭነቱ በሀገረ ካናዳ የሆነው ትኩረቱን በኢትዮጵያ ሀገራዊና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ አድርጎ የሚሰራው ሆርን ፍሪኩዌንሲ ሚዲያ በትናንትናው ዕለት ዘግቧል።

ሚዲያው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዲፕሎማቲክ እና የደኅንነት ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ ይፋ ባደረገው መረጃ የቱርክ የመረጃ እና ደኅንነት ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ በገፍ እየገቡ እና ለስለላ ተግባራት ወደተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች እየተሰማሩ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን ጨምሮ ከሰሞኑ በብዛት ገብተዋል የተባሉት የቱርክ የደኅንነት ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት በቆጵሮስ ፓስፖርት መሆኑን በዘገባው ላይ የሰፈረው መረጃ ያመላክታል።

የደኅንነት ባለሙያዎቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ማለትም በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ እንዲሁም በናዝሬት ከተሞች ተደጋጋሚ መዳረሻቸውን እንደሚያደርጉ ሆርን ፍሪኩዌንሲ ከዲፕሎማቲክ እና የደኅንነት ምንጮች ያገኘውን መረጃ መሰረት አድርጎ ዘግቧል።

በቆጵሮስ ፓስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በአዲስ አበባ ከተማ ተሰማርተዋል የተባሉት የቱርክ የመረጃ እና ደኅንነት ባለሙያዎች ማረፊያቸውን በመዲናዋ በተለየ ሁኔታ ቦሌ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኙ ሆቴሎች እና የእንግዳ ማረፊያዎች ማድረጋቸውም ተነግሯል።

የደኅንነት ባለሙያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ለጥናታዊ ፅሁፍ ዝግጅት የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ባለሙያዎችን ቃለምልልስ የሚያደርጉ ተመራማሪዎች እንዲሁም የመንግሥት ፕሮጀክቶችን የሚጎበኙ እና የሚዲያ ሽፋን የሚሰጡ ጋዜጠኞችን ሆነው እንደሆነ ዘገባው ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።

ይሄንን ተከትሎ ዞብል ፖስት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማጣራት ያደረገ ሲሆን፣ የቱርክ መንግሥት የነፃ ትምህርት ዕድል ከሚሰጣቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ለመረጃ እና ደኅንነት ስራ እንደሚመለምል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለመጽሔታችን ገልጸዋል።

እኒሁ ለቱርክ መንግሥት የመረጃ እና ደኅንነት ስራዎችን እንዲሰሩ የሚመለመሉ ኢትዮጵያውያን በቱርክ ሀገር የሚከታተሉትን ትምህርት እና የመረጃ እና ደኅንነት ስልጠናቸውን ሲጨርሱ በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ እንዲሁም በተራድኦ ድርጅቶች ውስጥ እንዲሰማሩ እንደሚደረግ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አክለው አስረድተዋል።

ዓለም ላይ ካሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪዎች አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው እና በኦቶማን ዘመን የነበረውን የቱርክን የቀደሞ ገናናነት ለመመለስ እየሰሩ ነው የሚባሉት ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የጅኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት እስልምናን ዋነኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊስ ማዕከል ማድረጋቸውን በርካታ የዓለምአቀፍ ግንኙነት እና የአካባቢ ጥናት ተንታኞች ሲናገሩ ይደመጣል።

ለምሳሌ ያህል በሎንደን ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ እና የዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አህመት ኤርዲ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በጥቅምት 2024 በሎንደኑ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ቤት ድረ-ገፅ ላይ “Transnationalisation of Turkish Islam: Navigating Global Influence Through Faith” በሚል ርዕስ ያወጡት ፅሁፍ ኤርዶጋን እስልምናን የውጭ ግንኙት ፖሊሲያቸው ቀዳሚ ማጠንጠኛ ማድረጋቸውን ያትታሉ።

ከዚሁ ጋር በተገናኜ በሶማሊያ ከዓመታት በፊት ተከስቶ የነበረውን ከባድ ርሃብ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን የቱርክ ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩበት ወቅት በፈረንጆቹ 2011 ዓ.ም ሶማሊያን በመጎብኘትና ለርሃብ ለተጋለጡ ሶማሊያውያን አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ በምላሹ በሞቃዲሾ ከተማ አቅራቢያ “ካምፕ ቱርክሰም” የተሰኘ ግዙፍ የጦር ሰፈር እና ወታደራዊ ማሰልጠኛ መገንባት መቻላቸው ይታወሳል።

ከዚህም በተጨማሪ በኦቶማን ጊዜ በቱርክ ግዛት ስር የነበረውን የሱዳኑን ሱዓኪን ወደብ ለማልማት በፈረንጆቹ 2017 ዓ.ም ኤርዶጋን እና የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አል በሽር ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ የወደብ ልማት ስምምነት ተፈራርመው እንደነበር አይዘነጋም። ስምምነቱ በሱዳን የተከሰተውን አብዮትና የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ተፈፃሚ ሳይሆን ቀርቷል።

እስልምናን ለውጭ ግንኙነት ፖሊስ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ከምትጠቀመዋ እና በርካታ የመረጃ እና ደኅንነት ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ እያስገባች መሆኑ ከተነገረላት ቱርክ ጋር በተያያዘ፣ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ በሚከሰቱ ሐይማኖት ተኮር ውጥረቶች ጣልቃ እንደምትገባ በርካቶች አስተያየታቸውን ሲሰጡ የሚስተዋል ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተገናኘ ሀገሪቷ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮች ዙሪያ ስታራምድ የነበረው አቋም ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የቱርክ የመረጃ እና ደኅንነት ባለሙያዎች በብዛት ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ቀጠናዊ እና ጅኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎትን በሐይማኖት ተኮር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከማስፈፀም ጋር የተገናኘ አንደኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሆርን ፍሪኩዌንሲ ካወጣው መረጃ በመነሳት መላምት ማስቀመጥ ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ በዋናነት በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በራስ ገዟ ሶማሌላንድ፣ እና በሶማሊያ መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ባሉ ቀጠናዊ ለውጦች ምክንያት ቱርክ “ባላንጣዬ” ከምትላቸው እንደ እስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች ካሉ ሀገራት ጋር ካላት ጅኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻ ጋር በተገናኘ የመረጃ እና ደኅንነት ባለሙያዎቿን በኢትዮጵያ ልታሰማራ እንደምትችል ይገመታል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች