ታሕሣስ 15/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
ህወሓት የሰው አልባ የውጊያ አውሮፕላን ተቆጣጣሪዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ህወሓት በተለምዶ “ድሮን” ተብሎ የሚጠራውን የሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላን ተቆጣጣሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑ የተነገረው በሱዳን ከሚገኙት ታጣቂዎቹ መካከል ለተመረጡ አባላቱ መሆኑን የመረጃ ምንጫችን አያይዘው ጠቅሰዋል።
የሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላን ተቆጣጣሪዎች ስልጠናው የሚሰጣቸው በገዳሪፍና ከሰላ መካከል በሚገኘው “ሽዎክ” ተብሎ በሚጠራ የሱዳን ግዛት ውስጥ መሆኑን ጉዳዩን አስመልክቶ ለመጽሔታችን የደረሰው ዝርዝር ያሳያል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላን ተቆጣጣሪ ሰልጣኞቹን ያቀፈው ቡድን ከሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖች አብራሪነት እስከ የአየር ጥቃት አክሻፊዎችን ያካተተ ስለመሆኑ ተነግሯል።
እንደ ዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች አሰልጣኞችን በመመደብ እና አጠቃላይ የስልጠና ቁሳቁስ ግብዓቶችን በማቅረብ የግብፅ መንግሥት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ ስልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙት የሰው አልባ አውሮፕላን ተቆጣጣሪዎች በያዝነው ታሕሣስ ወር መጨረሻ ስልጠናቸውን ጨርሰው ይመረቃሉ ተብሏል።
በሱዳን የሚገኘው የህወሓት ታጣቂ ክንፍ እንደ ሀሸባ፣እንጉርጉር፣ ተነድባ፣ ግዴማ ፣ስፋዋ ተብለው ከሚጠሩ የስደተኛ ጣቢያዎች ጭምር ታጣቂዎችን እንደሚመለምል ትኩረታቸውን የሱዳን ጦርነት ላይ ያደረጉ በርካታ የሚዲያ ተቋማት ዘገባዎች እና የጥናት ተቋማት የምርምር ውጤቶች ያሳያሉ።
በሱዳን የሚገኙት የህወሓት ተዋጊዎች በሀገሪቷ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት በጄኔራል አልቡርሃን የሚመራውን የሱዳን ብሔራዊ ጦር ተቀላቅለው በሲንጃ፣ ሲናር፣ ሀሳሂሳ፣ መደኒ፣ አልባጌር ፋው፣ እና ደንበልያ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች በተካሄዱ አውደ ውጊያዎች መሳተፋቸውን ዞብል ፖስት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያገኘው መረጃ ያሳያል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ተፈርሞ የነበረው የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ተግባራዊ አለመደረጉን እና ስምምነቱን የሚጥሱ የተለያዩ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መታየታቸውን ተከትሎ፣ በርካቶች ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ይስተዋላል።
ግምቶች ወደ እውነትነት ተቃርበው በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ዳግም ጦርነት የሚቀሰቅስ ከሆነ፣ ህወሓት በስልጠና ላይ የሚገኙትን የሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላን ተቆጣጣሪዎችን ጨምሮ በሱዳን ለሚገኙት ታጣቂዎች ወታደራዊ ግዳጅ ሊሰጥ እንደሚችል ይጠበቃል።


