ታሕሣስ 24 2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት 12 ኮንቴይነር የጦር መሳሪያ ግዥ መፈፀሙን ዞብል ፖስት መጽሔት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ያገኘው መረጃ ያሳያል።
የክልሉ መንግሥት የጦር መሳሪያ ግዥውን ከፈፀመ በኋላ ከጅቡቲ ወደብ በመረከብ በያዝነው የታሕሣስ ወር አጋማሽ በተሳቢ መኪኖች አጓጉዞ ወደ ክልሉ እንዲገባ ማድረጉን መረጃውን ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።
የጦር መሳሪያ ግዥው ከተፈፀመ በኋላ በ12 ኮንቴይነሮች ተጭኖ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ታጅቦ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንዲረከብ መደረጉን ዞብል ፖስት ያገኘው መረጃ ያሳያል።
የክልሉ መንግሥት ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ግዥ መፈፀሙን በማስታወስ፣ ከዚህ በፊት የተገዛው የጦር መሳሪያ ከኢትዮጵያ ጅቡቲ በተዘረጋው የባቡር ሀዲድ በኩል በባቡር ተጓጉዞ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲገባ መደረጉን መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል በመመልመል ተከታታይ ወታደራዊ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ከክልሉ የፖለቲካዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዘው የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይሄንን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ የተረከበው እና ከዚህ ቀደም የፈፀማቸው የጦር መሳሪያ ግዥዎች ዋነኛ ዓላማ በቁጥር እየጨመረ ከመጣው የክልሉ ወታደራዊ ኃይል ጋር ተመጣጣኝ የጦር መሳሪያ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል ነው ተብሎ ይገመታል።
የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች እንደገለፁት፣ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አዳዲስ ጦር መሳሪያ ግዥዎችን እየፈፀመ የሚገኘው የክልሉን የፀጥታ መዋቅር በሜካናይዝድ ጦር እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ለማጠናከር ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ መዋቅሩን ለማጠናከር አገልግሎት ላይ ያውላቸዋል የተባሉትን የሜካናይዝድ ጦር መሳሪያዎች እና ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጭ ሌላ የክልል ፀጥታ መዋቅር ሊታጠቅም ሆነ ሊገለገልባቸው እንደማይችል የሚታወቅ ነው።
መጽሔታችን የጦር መሳሪያ ግዥው ከዬት ሀገር እንደተፈፀመ ለማወቅ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ “የኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ጊዜያት የጦር መሳሪያ ግዥዎችን ከመፈፀሙ በዘለለ የግዥውን ዝርዝር ሂደት አላውቅም!” ሲሉ የመረጃ ምንጫችን ለዞብል ፖስት ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።


