ጥር 3 2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን አስተዳደር ለሁለት የዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ማስተላለፉን የዞኑ አስተዳደር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የዞኑ አስተዳደር ይሄንን ውሳኔ ለማስተላለፍ የተገደደው የተራድኦ ድርጅቶቹ ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች፣ ስልጠናዎች፣ እና ልዩ ልዩ ተግባራት ከግብረሰናይ እንቅስቃሴ እና ሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት በሚፃረር መልኩ የዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያን ሕግጋቶች በመጣስ ለህወሓት ፖለቲካዊ ወገንተኝነትን ሲያሳዩ እና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በመገኘታቸው ነው ብሏል።
ወልቃይትን እና አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው ሁለቱ የተራድኦ ድርጅቶች Norwegian Refugee Council (NRC) እና International Medical Corps (IMC) ሲሆኑ፣ ከዚህ ውሳኔ ቀደም ብሎ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንደነበር የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን አስተዳደር ባወጣው መግለጫ አያይዞ ገልጿል።
በሕገ-ወጥ ተግባራት በመሰማራታቸው ከአካባቢው እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው የተራድኦ ድርጅቶቹ በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅሬታን የሚፈጥሩ እና ሌሎች የግብረሰናይ ድርጅቶች በጥርጣሬ እንዲታዩ የሚያደርጉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የቆዩ ሲሆን፤ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የተሰጣቸውን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተፈፃሚ ባለማድረጋቸው ከአካባቢው እንዲወጡ ውሳኔ ለማስተላለፍ ተገድጃለሁ ሲል የዞኑ መንግስት በመግለጫው ላይ አስታውቋል።
ከወልቃይት ጠገዴ ለቅቀው እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሁለቱ የተራድኦ ድርጅቶች “ከተቋቋሙለት የሰብዓዊ ድጋፍ ዓላማ በተቃረነ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ለዘመናት ሲያደርግ የኖረውን የነፃነት ተጋድሎ እና በብዙ መስዕዋትነት ያገኘውን ነፃነት ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ትግል እንደ አፈናቃይ አድርገው ሲገልፁ ቆይተዋል” ሲል ዞኑ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የስራ ቅጥር ሲያወጡም ሆነ ሌሎች ይፋዊ ግንኙነቶችን ሲያደርጉ አካባቢውን የትግራይ ክልል አካል እንደሆነ አድርገው እና ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንኳን “አወዛጋቢ አካባቢዎች” ብሎ የሚጠራውን ወልቃይት ጠገዴ ከአካባቢው ለቅቀው እንዲወጡ የተወሰነባቸው የተራድኦ ድርጅቶቹ ግን “ምዕራብ ትግራይ” እያሉ በመጥራት ለህወሓት ግልጽ ፖለቲካዊ ውግንና ሲያሳዩ መቆየታቸውን የዞኑ አስተዳደር በዛሬው ዕለት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አያይዞ አስታውቋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን አስተዳደር በሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ለተገኙት ለሁለቱ የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች አካባቢውን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ የሰጠ ቢሆንም፣ ሕግን አክብረው ለተቋቋሙለት የሰብዓዊ ድጋፍ እና ግብረሰናይ አገልግሎት ለመስጠት በአካባቢው ከተሰማሩ ሌሎች ሀገር በቀልም ሆኑ ዓለምአቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን በመግለጫው አክሎ ገልጿል።
ዞብል ፖስት መጽሔት ባሳለፍነው ሰኔ 2017 ዓ.ም “በጠለምት የሚንቀሳቀሱ የተራድኦ ድርጅቶች በአካባቢው የሚፈፅሙት ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት እና ለጦርነት ድግሥ የሚጫወቱት ሚና” በሚል ርዕስ ሰፊ የምርመራ ዘገባ መስራቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ልክ እንደ ወልቃይት ጠገዴ ሁሉ በጠለምት የሚገኙ በርካታ የተራድኦ ድርጅቶችም ከሰብዓዊ ድጋፍ ውጭ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጣልቃገብነት በመፈፀም ላይ እንደሚገኙ ማጋለጣችን አይዘነጋም።


