የጅቡቲ መንግሥት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የላቸውም ያላቸውን በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ጠርንፎ ሊያባርር መሆኑ ተሰምቷል። በጅቡቲ ለመቆየት የተሰጣቸውን የመጨረሻ የጊዜ ገደብ ጨርሰው አሁንም ድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን፣ የጀቡቲ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከያሉበት እያሰሱ በመያዝ በጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያዎች ማሰር መጀመራቸውን የደረሰን መረጃ ያሳያል።
በሀገሪቱ ሃምሳ ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ በጉልበት ስራ፣ በጉሊት ንግድ፣ እንዲሁም በቤት ሰራተኝነት የሚተዳደሩ ናቸው። ከዚህ ቀደም በጅቡቲ የሚኖሩ ህገ-ወጥ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሀገሪቱ መንግሥት የሶስት ወራት የማስጠንቀቂያ ጊዜ ሰጥቶ ነበር። የተሰጠው የጊዜ ገደብ በፈረንጆቹ ግንቦት 3፣ 2025 ዓ.ም መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ጠርንፎ የመመለስ እንቅስቃሴ በይፋ መጀመሩን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያመላክታል።
በያዝነው ግንቦት ወር መጀመሪያ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የተሰጠውን የማስጠንቀቂያ የጊዜ ገደብ ተከትሎ፣ “ጋላፊ እና ደዋሌ” ተብለው በሚጠሩ የድንበር አካባቢዎች አቋርጠው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን “All East Africa” የተሰኘ ድረ-ገፅ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን እና የተራድኦ ድርጅት ሠራተኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቦ ነበር።
የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ ሶስት ሳምንታት ያለፉ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ይገኛሉ። ይህንን ተከትሎ፣ የጀቡቲ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ህገ-ወጥ ያሏቸውን በርካታ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ጠርንፎ ለመመለስ እንዲያመቻቸው፣ ከያሉበት እያሰሱ በመያዝ ወደ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያዎች ማጋዝ ጀምረዋል።
ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ለረዥም ዓመታት መልካም የሚባል የትብብር፣ ጉርብትና፣ እና ወዳጅነት ታሪክ የነበራቸው ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መላላት በመፈጠር ላይ ይገኛል።
የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከጅቡቲ በተጨማሪ፣ የወደብ እና የባህር በር አማራጮችን የማፈላለግ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ፣ በሁለቱ ሀገራት ለተፈጠረው የጉርብትና መሻከር በምክንያትነት ይጠቀሳል።
“ጅቡቲ በርካታ ኢትዮጵያውያን ህገ-ወጥ ናችሁ በሚል ባልተለመደ ሁኔታ ከግዛቷ ለማባረር የወሰነችው፣ በዚሁ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተፈጠረው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መላላት ምክንያት ነው” ሲሉ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ፖለቲካ አስተያየታቸውን የሚያጋሩ ምሁራን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ወዲህ ባሉት ቅርብ ዓመታት፣ ኢትዮጵያ በምትከተለው “ግለሰብ-መር” የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምክንያት፣ ጅቡቲን ጨምሮ ከሌሎቾ የጎረቤት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረት እየነገሰበት ይገኛል። ጅቡቲ በግዛቷ የሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን “ባልተለመደ ሁኔታ” ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መወሰኗ የዐቢይ አህመድ መንግሥት አንዱ ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል የተፈጠረውን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር ተከትሎ፣ ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ዙሪያ ተፅዕኖዋን የሚያሰፋ “አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ” የተባለለትን ስምምነት ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ከጅቡቲ ጋር መፈራረሟ የሚታወስ ነው።