Saturday, May 9, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው በገራዶ የተፈናቃዮች ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች...

ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው በገራዶ የተፈናቃዮች ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች አካባቢው ለልማት ይፈለጋል በሚል የሚኖሩባቸው ድንኳኖች እየፈረሱባቸው እንደሆነ ተናገሩ

በ2014 ዓ.ም ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደቡበ ወሎ ዞን፣ ገራዶ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ አማራጭ ስፍራ ሳይዘጋጅላቸው “አካባቢው ለልማት ተፈልጓል” በሚል የተጠለሉባቸው ድንኳኖች እየፈረሱባቸው መሆኑ ታውቋል። 

ከሶስት ዓመታት በፊት ከኦሮሚያ ክልል ከተፈናቀሉ በኋላ፣ በገራዶ መጠለያ ጣቢያ በርካታ ሰዎች በድንኳኖች ውስጥ ለረዥም ጊዜ ይኖሩ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን በመንግሥት ባለስልጣናት “ቦታው መልማት ስላለበት ለባለሀብት ተሰጥቷል” መባላቸውን ዞብል ፖስት ከአካባቢው ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ተፈናቃዮቹ ተጠልለውበት የነበረውን ስፍራ “መልማት አለበት” በሚል እንዲፈርስ እየተደረገ ያለው፣ በስፍራው ለሚገኙ በርካታ ተፈናቃዮች ምንም አይነት ተለዋጭም ሆነ ተተኪ መጠለያ ቦታ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ነው።

ቦታውን ለማልማት ተረክበዋል የተባሉ አካላት መጠለያዎችን ለማፍረስ በመጡበት ወቅት፣ ተፈናቃዮቹ በጉዳዩ ላይ የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባን ለማናገር ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አለመቻሉን፣ DW የአማርኛው ክፍል በትናንትናው ዕለት ተፈናቃዮቹን አነጋገሮ ያጠናቀረው ዘገባ ያሳያል።

በጉዳዩ ዙሪያ ለDW አስተያየት የሰጡት “የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ” አቶ መሐምድ ሰዒድ፣ “የከተማ አስተዳደሩ እርማጃውን ከመውሰዱ በፊት ተለዋጭ ቦታ ማዘጋጀት ነበረበት” በማለት፣ ተፈናቃዮቹ “ቦታውን ልቀቁ” መባላቸውን የሚያሳይ የአቤቱታ ማመልከቻ ለጽ/ቤታቸው እስካስገቡበት ቀን ድረስ ጉዳዩን እንደማያውቁት የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል።

ዞብል ፖስት የገራዶ ተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ መፍረሱን ተከትሎ ባደረገው ተጨማሪ የማጣራት ስራ፣ በደሴ ከተማ ውስጥ፣ የመንግስት መስርያ ቤት ሆነው ያገለግሉ የነበሩ ቦታዎች፣ የቀበሌ ቤቶች፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት ቦታዎች፣ የቀድሞ የዕርዳታ እህል ማስቀመጫ ቦታዎች፣ እንዲሁም የአረንጓዴ ስፍራዎች በመንግስት ባለስልጣናት ተሸጠው ማለቃቸውን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ያልጠቀስናቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የደሴ ከተማ ነዋሪ፣ “ከላይ ከተጠቀሱት የተሸጡ ቦታዎች በተጨማሪ፣ ከሰባት መቶ በላይ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ገራዶ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ለባለሀብት በከፍተኛ ገንዘብ ተሸጧል” በማለት መረጃውን ለዞብል ፖስት አጋርተዋል።

ያነጋገርናቸው የደሴ ከተማ ነዋሪ አክለውም፣ “ከሰባት መቶ በላይ የሚሆኑትን የወለጋ ተፈናቃዩች ሜዳ ላይ የሚበትን ውሳኔ ያሳለፉት አካላት፣ ከዚህ ቀደም የደሴ ከተማን መሬት ያለ ጨረታ እና ያለ ተጠያቂነት በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ በድርድር ሲሸጡ የቆዩት ባለስልጣናት ናቸው” በማለት ጉዳዩን በዝርዝር አስረድተዋል።

ዞብል ፖስት “በተፈናቃዮቹ የመጠለያ ስፍራ መፍረስ እና በከተማዋ እየተፈፀመ ነው ስለተባለው ህግን ያልተከተለ የመሬት ሽያጭ ዙሪያ፣ የደሴ ከተማ አስተዳደር ምን ይላል?” የሚል ጥያቄ ለማቅረብ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ የእጅ ስልክ ደጋግመን የደወልን ቢሆንም ከንቲባው ስልካቸውን ሊያነሱ አልቻሉም።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች