Saturday, May 2, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባዔ የአቶ አገኘሁ ተሻገርን ቦታ ተክተው እንዲሰሩ ተደረገ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባዔ የአቶ አገኘሁ ተሻገርን ቦታ ተክተው እንዲሰሩ ተደረገ።

ሐምሌ 9/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና! 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ ዑመድ የአቶ አገኘሁ ተሻገርን የዋና አፈጉባኤነት ቦታ ተክተው እንዲሰሩ መደረጋቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት አስረድተዋል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ ባሳለፍነው ሰኔ ወር በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ተመትታ በጎርጎር በወደቀችው ሔሊኮፕተር ውስጥ ተሳፍረው እንደነበር እና አንገታቸው አካባቢ ጉዳት እንደደረሰባቸው በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አቶ አገኘሁ ተሻገር ጉዳት ባስተናገዱበት የጎርጎራው ሔሊኮፕተር ሌላኛው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ወታደራዊ ባለሥልጣን ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ እና በአደጋው ህይወቱ ያለፈው የኢዜአ ጋዜጠኛ አንድ ላይ ተሳፍረው እንደነበር አይዘነጋም።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ በቅድሚያ በጦር ኃይሎች ሆስቲታል ሕክምና ሲደረግላቸው የቆዩ ሲሆን የጤናቸው ሁኔታ መሻሻል ባለማሳየቱ ለተሻለ ሕክምና ወደ ውጭ መላካቸውን መረጃውን ያደረሱን ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል። 

ይሄንን ተከትሎ የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ ዑመድ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ተክተው እንዲሰሩ መደረጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለመፅሔታችን ገልጸዋል።

ሆኖም፣ በምክር ቤቱ የሚሰሩ የኦሮሞ ተወላጅ አመራሮች እና ሙያተኞች ቦታው ለእኛ ይገባል በሚል ወይዘሮ ዘሃራ ዑመድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ቦታን ተክተው እንዲሰሩ በመደረጋቸው ቅሬታ እያሰሙ ነው ተብሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የ2018 ዓ.ም የበጀት ድልድልን አስመልክቶ የምክር ቤቱ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ተረፈ በዳዳ ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን መረጃ እንዲሰጡ ጥያቄ ቀርቦላቸው “አፈጉባኤ ሆነው እየሰሩ ያሉትን ወይዘሮ ዘሃራን ጠይቁ” የሚል የኩርፊያ ምላሽ መስጠታቸውን መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች