ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ከዓለምአቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች የሚቀርቡ የሰብዓዊ እርዳታዎች ለተረጅዎች በአግባቡ እየደረሱ አለመሆኑን በክልሎቹ የሚንቀሳቀሱ የረድኤት ድርጅት ሠራተኞች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
ለመጽሔታችን በደረሰው መረጃ መሰረት በሁለቱ ክልሎች በርካታ የሰብዓዊ እና አስቸኳይ የምግብ እርዳታን የሚፈልጉ ዜጎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከተራድኦ ድርጅቶቹ የሚቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ ግን በሚጠበቀው ልክ ለተረጂዎች በአግባቡ እየደረሰ አለመሆኑ ተነግሯል።
ለአብነት ያህል፣ በትግራይ ክልል ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚቀርቡ የምግብ እና ቁሳቁስ ድጋፎች ላይ የክልሉ ባለሥልጣናት ለህወሓት ታጣቂዎች ፍጆታ በሚል ከተረጅዎች ላይ በየጊዜው እንደሚወሰዱ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የረድኤት ድርጅት ሠራተኛ ለዞብል ፖስት ያደረሱት መረጃ ያሳያል።
በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ክፍፍል በሚደረግበት ወቅት ለህወሓት ታጣቂዎች በሚል ከተረጅዎች ድርሻ ላይ በየጊዜው ይሰበሰባል ሲሉ በክልሉ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ መረጃውን ለዞብል ፖስት ያደረሱት የረድኤት ምንጮች አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም የዓለምአቀፍ ረድኤት ድርጅቶች እህል እና ሎጅስቲክ ማከማቻ መካዝኖች በህወሓት ታጣቂዎች ዝርፊያ ሲፈፀምባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከተረጅዎች ድርሻ ላይ ለታጣቂዎች ቀለብ በሚል እየተወሰደ ይገኛል።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል ከተራድኦ ድርጅቶች የሚቀርበውን የሰብዓዊ ድጋፍ የወረዳ ባለሥልጣናት ተረጅ ላልሆኑ ዘመድ አዝማዶቻቸውና ለቅርብ ቤተሰቦቻቸው እንዲሰጥ እንደሚያደርጉ እና እርዳታን ለሚጠባበቁ ወገኖች መሰጠት ያለበት ድጋፍ በአግባቡ እንደማይቀርብላቸው ለመጽሔታችን የደረሰው የጥቆማ መረጃ ያመላክታል።
ከዚህም በተጨማሪ በአማራ ክልል የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚቀርቡ እርዳታዎችን እየወሰዱ እንደሚሸጡ ዞብል ፖስት ከረድኤት ድርጅት ሠራተኞች ያገኘው መረጃ ያሳያል። ይሄንን ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተረጅዎች ለከፍተኛ አደጋ እየተጋለጡ ነው ተብሏል።
በአማራ ክልል ዋግህምራ፣ ጠለምት፣ በየዳ፣ በለሳ እና እብናት ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች የሚገኙ ተረጅዎች የክልሉ ካድሬዎች እና የፀጥታ አካላት በሰብዓዊ እርዳታዎች ላይ በሚፈፅሙት ተግባር ምክንያት ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየተፈጠረ መሆኑ ተነግሯል።
በድርቅ፣ በጦርነት፣ በመፈናቃል እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በኢትዮጵያ ከሃያ አምስት ሚሊዮን ያላነሱ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታትን እና ሌሎች ተቋማት ያወጧቸው ሪፖርቶች የሚያመላክቱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ይገኛሉ።
እንዲያም ሆኖ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ የሰብዓዊ ድጋፍ ተረጅዎች ከተራድኦ ድርጅቶች የሚቀርብላቸውን እርዳታ በአግባቡ እያገኙ አለመሆኑን ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው የተራድኦ ድርጅት ሠራተኞች ያገኘው መረጃ ያሳያል።


