መስከረም 20/2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር የኢሬቻ በዓልን ለሚያከብሩ የመንግሥት ሠራተኞች የባህል አልባሳት ወጫቸውን እንዲሸፈን መወሰኑን ዞብል ፖስት ያገኘው መረጃ ያሳያል።
የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር ስር በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የመንግሥት ሠራተኞች ለኢሬቻ በዓል የሚያስፈልጋቸውን የአልባሳት ወጭ እንዲሸፈን ማድረጋቸው ተነግሯል።
ለዚሁ ሲባል የከተማ መሥተዳድሩ 275 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለበዓል አልባሳት ወጪ ማድረጉን መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል የሚያስተባብር ኮሚቴ በልደታ ክፍለ ከተማ ስር የተቋቋመ ሲሆን፣ በከተማዋ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ወጪ ከከተማዋ ባለሃብቶች በመሰብሰብ ለመሸፈን እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም።
የወይዘሮ አዳነች አቤቤ አሥተዳደር በበኩሉ በበዓሉ ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የባህል አልባሳት ወጪ በአዲስ አበባ ከተማ መሥተዳድር እንዲሸፈን ማድረጉ ተገልጿል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መንግሥት “የኦሮሞ ባህል ሕዳሴን አውጃለሁ” ብሎ ለትግበራው እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን፣ ይሄንኑ የመንግሥት ዕቅድ በኢሬቻ በዓል ላይ ለማንፀባረቅ በኮሚቴ ደረጃ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል።


