Saturday, May 23, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮች"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ አልቀበልም" የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ!

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ አልቀበልም” የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ!

ጥር 23 2018 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት ወር ለሚያካሂደው ሠባተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞንን በምዕራብ ትግራይ ምድብ ስር እንዲሆን የሰጠውን ውሳኔ አልቀበልም ሲል ውድቅ አድርጓል።

ኮሚቴው የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱን ውሳኔ ውድቅ ያደረገው ዛሬ አመሻሹን ባወጣው መግለጫ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት 24 2018 ዓ.ም ለማካሄድ ባቀደው አገራዊ ምርጫ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በአማራ ክልል ሥር እንዲመደብ በመግለጫው ጠይቋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ ህወሓት ከሕግ አግባብ እና ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ ለሦስት አሥርት ዓመታት በጉልበት ወደ ትግራይ አካልሎት የኖረው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ “እኛ አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም” በሚል የትግል መሪ ቃል በ2008 ዓ.ም ለፌደሬሽን ምክር ቤት የወሰንና ማንነት ጥያቄውን ከማስገባት ጀምሮ በተደረገው ትግል ሕዝቡ ላለፉት 5 ዓመታት ነፃነቱን ማግኘቱን በመጥቀስ፣ ምርጫ ቦርዱ ይሄንን ከግምት በማስገባት ውሳኔውን በአስቸኳይ እንዲያስተካክል ጥሪ አቅርቧል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ በመግለጫው አያይዞም፣ በቀድሞው የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ በአቶ አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ እና አካባቢ በአካል ተገኝቶ ካደረገው የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ጀምሮ አሁን እስካለው አሥተዳር ድረስ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ ምርጫ ቦርዱ ማሳለፉን ገልጿል።

ኮሚቴው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ በአማራ ክልል ስር እንዲመደብ በማሳሰብ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ መልሶ በማጤን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ በመግለጫው ጠይቋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ የሕዝቡ ማንነት እንዲከበር እና ታሪካዊ ወሰኑ እውቅና እንዲሰጠው በጠዬቀበት መግለጫ በመጪው አገራዊ ምርጫ በአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ሲከናወን በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አያይዞ ገልጿል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች