ጥር 28 2018 ዓ.ም—ዞብል ፖስት ዜና!
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸው ባሳለፍነው ማክሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ስለተፈጠረው ፀብ አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ለቀረበላቸው የምስክርነት ጥሪ በዛሬው ዕለት በደብዳቤ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥር 26 2018 ዓ.ም በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ “በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ችግር የተፈጠረው ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በማንሳቷ ምክንያት ሳይሆን በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል በነበረው ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፎ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ዝርፊያን እና ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈፀማቸው ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አያይዘውም፣ “ሕዝቤን አታጎሳቁሉ” የሚል መልዕክት አስይዘው ገዱ አንዳርጋቸውን ወደ ኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ መላካቸውን እና “ገዱ ህሊና አላቸው፣ ክር አላቸው፣ ኤርትራ በሄዱበት ወቅት ምን እንደመከሩ ሊመሰክሩ ይችላሉ” ሲሉ ገዱ አንዳርጋቸው በጉዳዩ ላይ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ጠይቀው ነበር።
ገዱ አንዳርጋቸውም ጠቅላይ ሚንስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ፊት ላቀረቡት የምስክርነት ጥሪ በዛሬው ዕለት ለሚዲያ አካላት ባሰራጩት ባለ ሦስት ገፅ ደብዳቤ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረውን ፀብ አስመልክቶ “ጠቅላይ ሚንስትሩ ስለ እኔ የተናገሩት ሃሰት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ገዱ አንዳርጋቸው “በእኔ በኩል ያለው እውነት” ብለው ባቀረቡት ምላሽ ላይ፣ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን የያዘ መልዕክት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ተቀብለው በ2013 ዓ.ም በጥር ወር መጀመሪያ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ማድረሳቸውን የገለፁ ሲሆን፣ ያደረሱትን መልዕክትም በደብዳቤያቸው ላይ በዝርዝር አስፍረዋል።
በወያኔ ላይ በጋራ በተወሰደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ለድል በመብቃታችን የእንኳን ደስ አለህ የደስታ መግለጫ ለፕሬዘደንት ኢሳያስ ማስተላለፍ፣ የሰሜን ዕዝ ጥቃት በደረሰበት ወቅት ሰራዊቱን ተቀብለው ላደረጉለት እንክብካቤ እና ኋላም ለመልሶ ማጥቃት እንዲዘጋጅ ላደረጉልን ወንድማዊ ድጋፍ ለኤርትራ መንግስት እና ሕዝብ ምስጋና ማቅረብ፣ እና አንዳንድ የወያኔ ደጋፊዎች እና የኢትዮጵያን እና የኤርትራን መልካም ግንኙነት የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሚዲያዎች አማካኝነት ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በከፈቱት ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሊደረግ ስለሚገባው የጋራ ጥንቃቄ ማብራራት እንደነበሩ ገዱ አንዳርጋቸው በደብዳቤያቸው አብራርተዋል።
ገዱ አክለውም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚቀርቡትን እነዚህን መልክቶች ከገለፁልኝ በኋላ በእሳቸው በኩል “ጦርነቱ መጠናቀቁን በይፋ ለሕዝብ ማሳወቃችንን ተከትሎ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየጠየቀን ያለውም የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ እንዲወጣ በመሆኑ ለምን የኤርትራ መንግስት ሰራዊቱን እንዲያስወጣ በግልፅ አንነግራቸውም?” የሚል ጥያቄ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ማቅረባቸውን በማስታወስ ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን ገልፀዋል።
ገዱ አንዳርጋቸው ምላሽ ባሉት ደብዳቤ ላይ “ጠቅላይ ሚንስትሩ በመላ ሀገሪቷ በፊት አውራሪነት ከመሩት የሰው እልቂት፣ ንብረት መውደም፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅልና እና የሃገርን ህልውና ለሚፈታተን ቀውስ ራሳቸውን ነፃ አድርገው ሌላ ተጠያቂ መፈለጋቸው ኢትዮጵያ ካለችበት ሀገራዊ ቀውስ የከፋ ሌላ አዲስ ቀውስ ለመፍጠር እየተንደረደሩ ነው” በማለት ስጋታቸውን ጭምር ገልፀዋል።


