Saturday, May 23, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እየገባ...

ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እየገባ እንደሚገኝ ተነገረ!

ጥር 30 2018 ዓ.ም ዞብል ፖስት ዜና! 

መነሻውን ከደቡብ ሱዳን ያደረገ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ድንበር ተሻግሮ ወደ ጋምቤላ ክልል እየገባ እንደሚገኝ ዞብል ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ያገኘው መረጃ ያሳያል።

መጽሔታችን ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ባለሥልጣናት እና የኢትዮጵያን ድንበር በተደጋጋሚ ጥሰው በመግባት ጥቃት እንደሚፈፅሙ የሚነገርላቸው የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ በማስተላለፍ ሂደቱ ተሳታፊ መሆናቸው ተነግሯል።

እነዚሁ የሕገ-ወጥ ጦር መሳሪያ አስተላላፊዎች ኢትዮጵያን እና ደቡብ ሱዳንን በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢያ ልዩ ስሙ “ፖቻላ” ተብሎ የሚጠራውን አካባቢ የሕገ-ወጥ ጦር መሳሪያ ሁነኛ ማስተላለፊያ መስመር አድርገው እንደሚጠቀሙበት የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

ከደቡብ ሱዳን የተነሳ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እየገባበት እንደሆነ በተነገረው በጋምቤላ ክልል ባሳለፍነው ኅዳር ወር የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለ ብሔር ተኮር ግጭት መቀስቀሱ የሚታወስ ሲሆን፣ በግጭቱ በርካታ ንፁሃን፣ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች፣ እንዲሁም የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው አይዘነጋም።

ዋና ከተማዋን ጨምሮ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ላይ የክልሉ መንግሥት የፀጥታ መዋቅር አባላት ተሳታፊ ናቸው ተብለው እንደሚጠረጠሩ ዞብል ፖስት ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ያገኘው መረጃ የሚያሳይ ሲሆን፣ ይሄንን ተከትሎ የክልሉ የአድማ ብተና እና የመደበኛ ፖሊስ አባላት የታጠቁትን የጦር መሣሪያ በጥር ወር 2018 ዓ.ም ገቢ እንዲያደርጉ ከክልሉ መንግሥት ማሳሰቢያ መተላለፉ ይታወሳል።   

በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በሚኖሩት የአኙዋክ እና ኑዌር ጎሳዎች መካከል ባለው ውጥረት ሳቢያ በጋምቤላ ክልል ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲከሰቱ የቆዬ ሲሆን፣ ከደቡብ ሱዳን ተነስቶ ወደ ጋምቤላ ክልል የሚተላለፈው የሕገ-ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውርም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጭ አያይዘው ገልጸዋል።  

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጋምቤላ ክልል ባሳለፍነው ኅዳር ወር ተቀስቅሶ እስከ ታኅሣሥ ወር ቀጥሎ በነበረውና የበርካቶችን ህይወት በቀጠፈው ግጭት ተሳትፈዋል የተባሉት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች አሁንም ድረስ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ መጽሔታችን ያገኘው መረጃ ያሳያል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች