Saturday, May 23, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeዜናዋና ዋና ዜናኤርትራ 12 ለሚጠጉ የሱዳን ታጣቂ ቡድኖች ወታደራዊ ስልጠና ትሰጣለች ተባለ።

ኤርትራ 12 ለሚጠጉ የሱዳን ታጣቂ ቡድኖች ወታደራዊ ስልጠና ትሰጣለች ተባለ።

መጋቢት 1 2018 ዓ.ም-ዞብል ፖስት ዜና!

ጄኔራል አል-ቡርሃን ከሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ጦር ጎን ተሰልፈው በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የሚሳተፉ ወደ 12 የሚጠጉ ታጣቂ ቡድኖች በኤርትራ መንግሥት እንደሚሰለጥኑ እና እንደሚታጠቁ “The Sudan Times” የተሰኘው የሚዲያ አውታር በዛሬው ዕለት ዘግቧል።

ሱዳንን ከግብፅ፣ ኤርትራ፣ እና ኢትዮጵያ ጋር የሚዋሰነውና በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚዘልቀው ምስራቃዊ ሱዳን፣ በአሁኑ ወቅት በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ለሚካሄደው ግጭት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ስፍራ እየሆነ መምጣቱን ከሱዳን የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ምስራቃዊ ሱዳን ከኤርትራ፣ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ጋር ድንበር ተሻጋሪ ትስስር ያላቸውን የተለያዩ ማንነቶች እና የጎሳ ማኅበረሰቦች የሚገኙበት አካባቢ ነው። በተጨማሪም አካባቢው ከጎረቤት ሀገራት ግጭቶች የተፈናቀሉ በርካታ ስደተኞችን የሚያስተናግድ እንደሆነ ይነገራል።

በእነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች የሱዳን ምሥራቃዊ ግዛቶች የበርካታ ታጣቂ ቡድኖች መፈልፈያ መሆኑን እና ድንበር ተሻገሪ ለቀጠናዊ ጦርነቶች መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል፣ ሱዳን ታዛቢዎችን እና የፖለቲካ ተንታኞችን አነጋግሮ ይዞት በወጣው ሰፊ ዘገባ አስነብቧል።

ዘገባው አክሎም፣ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበሩ ታሪኮች ለሱዳን አማፂያን እና የትጥቅ ንቅናቄዎች የስልጠና እና መጠለያ ስፍራዎችን በመፍቀድ ከግዛታቸው ተነስተው በሱዳን ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በማስታወስ ኤርትራ አሁን ላይ ለበርካታ ታጣቂ ቡድኖች ሰፊ ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ገልጿል።

ሱዳን ታይምስ አንድ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ተንታኝን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሏቸው ታጣቂ ቡድኖች መበራከት እና በጎሳዎች መካከል ያለው ጥልቅ የሥልጣን እና የሀብት ፉክክርን ተከትሎ፣ “ኤርትራ በርካታ ታጣቂ ቡድኖችን በማሰልጠን እና በማስታጠቅ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እጇን እንድታስረዝም ዕድል ፈጥሮላታል” ብሏል።

“ቀጣናው ለውጭ ሀገራት ሽኩቻ፣ በተለይም በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ላለው ውጥረት ተጋላጭ ሆኗል” ያለው የሱዳን ታይምስ ዘገባ፣ ምስራቃዊ ሱዳን ለቀጠናዊ የኃይል ፍልሚያዎች እና የውክልና ጦርነት “ምቹ ሜዳ” እየሆነ መጥቷል ብሏል።

በጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራውን የሱዳን ጦር (SAF) ደግፈው የሚዋጉ እና በኤርትራ ስልጠና እና ትጥቅ እያገኙ እንደሆነ የተነገረላቸው ሁሉም ታጣቂ ቡድኖች የተፈጠሩት የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከጀመረ በኋላ መሆኑንም ሱዳን ታይምስ አያይዞ ዘግቧል።

በኤርትራ መንግሥት ወታደራዊ ስልጠና እና ትጥቅ ከሚቀርብላቸው ታጣቂ ቡድኖች መካከልም የምስራቅ ሱዳን ነጻነት ንቅናቄ፣ የምስራቅ ኮርፕስ (Eastern Corps)፣ የምስራቅ ሱዳን ጋሻ ኃይሎች፣ የፍትህ እና ልማት ብሔራዊ ንቅናቄ ዋነኞቹ መሆናቸውን ሱዳን ታይምስ ባሰፈረው ዘገባ ተመላክቷል።

ይህ በኤርትራ የሚሰለጥኑ ሚሊሻዎች ቁጥር መጨመር ስጋት በፈጠረበት ወቅት፣ አሜሪካ ትናንትናው ዕለት የሱዳን ሙስሊም ወንድማማቾች (Muslim Brotherhood) ቡድንን በአሸባሪነት መፈረጇ የሚታወስ ሲሆን፣ በኤርትራ ይደገፋሉ ከተባሉት አብዛኛዎቹ ታጣቂ ቡድኖች በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች