መጋቢት 3 2018 ዓ.ም-ዞብል ፖስት ዜና!
እስራኤል በቅርቡ የሀገርነት እውቅና በሰጠቻት ሶማሌላንድ የውሃ ጠረፍ ላይ ስትራቴጂያዊ የጦር ሰፈር ለማቋቋም ዝግጅት እያደረገች እና የቦታ ልየታ ስራ እያከናወነች እንደምትገኝ ብሉምበርግ ዘግቧል።
ብሉምበርግ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናትን አነጋግሮ ባሰፈረው ሰፊ ሀተታ፣ እስራኤል ለማቋቋም ያሰበችው የጦር ሰፈር ከሶማሌላንድ ወደ ቀይ ባሕር መውጫ በኩል ባለ አካባቢ መሆኑን ዘግቧል።
ይህ ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ያስቻለው እስራኤል በፈረንጆቹ የታኅሣሥ ወር 2025 ዓመተ-ምህረት ላይ “ታሪካዊ ውሳኔ” ስትል የጠራችውን የሶማሌላንድ የሀገርነት እውቅና ተከትሎ ነው።
ሶማሌላንድ ከእስራኤል የሀገርነት እውቅን ካገኘች ከሁለት ወራት በኋላ ባሳለፍነው የካቲት ወር በእስራኤል ቴሌ-አቪቭ የኤምባሲ ግንባታ ስራዋን ማጠናቀቋን እና አምባሳደር መሾሟን ማሳወቋ ይታወሳል።
እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችውን እውቅና ተከትሎ፣ በቀይ ባሕር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ መጋጠሚያ ላይ ስልታዊ ወታደራዊ ይዞታን ለማግኘት የሚያስችል ትልቅ በር እንደከፈተላት ብሉምበርግ በዘገባው ላይ አስፍሯል።
የሶማሊላንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ከድር ሁሴን አብዲ ለብሉምበርግ እንደገለጹት፣ በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው ስልታዊ ግንኙነት በርካታ የደኅንነት ዘርፎችን ያጠቃልላል ብለዋል።
እስራኤል ከበርበራ ወደብ በስተምዕራብ በኩል 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ከፍተኛ ቦታ ላይ የጦር ሰፈር እና የደህንነት ተቋም ለመገንባት ጥናት ስታደርግ መቆየቷም ተረጋግጧል።
የጦር ሰፈር ይገነባበታል የተባለው ስፍራ ከየመን የሁቲ አማፅያን ይዞታ በባሕር በኩል 260 ኪሎ ሜትር ብቻ የሚርቅ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ እስራኤል ከገዛ ድንበሯ ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ሳያስፈልጋት የሁቲ አማፂያንን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርም ሆነ በቡድኑ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ለመፈፀም ያስችላታል ተብሏል።
ሃማስ እና ሂዝቦላህ በእስራኤል ከደረሰባቸው ጥቃት በኋላ የሁቲ አማፂያን ቡድን ለኢራን የቀራት ብቸኛ ጠንካራ አጋር ሲሆን፣ እስራኤል በሶማሊላንድ የምትገነባው የጦር ሰፈር የሁቲ ታጣቂዎችን በቅርብ ርቀት ለማጥቃት እና ለማዳከም ያመቻታል ተብሏል።
እስራኤል ቀድሞውንም በሐርጌሳ ከተማ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ለዲፕሎማሲያዊ እና ለደኅንነት ሥራዎች የሚያገለግሉ ክፍሎችን ተከራይታ እንደነበር ሲነገር መቆየቱ ይታወቃል።
ይህ የእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ በቀጠናው ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱ አይዘነጋም። ግብፅንና ኳታርን ጨምሮ 21 የአረብና የአፍሪካ አገራት ድርጊቱ የቀይ ባሕርን ሰላም ያናጋል በሚል ቁጣቸውን መግለፃቸው አይዘነጋም።
ከዚህም በተጨማሪም የእስራኤል በሶማሊላንድ መገኘት፣ በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት በኩል ከፍተኛ ተጽዕኖ ካላት ቱርክ ጋር ቀጥተኛ ፉክክር ውስጥ አስገብቷታል።
እስራኤል አሁን ላይ ቱርክን እንደ “አዲስ ባላንጣ” እና የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ተገዳዳሪ የምትመለከታት ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት የማይጣጣሙ ጅኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎቶች በቀጠናው አዲስ የኃይል ሚዛን እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያል።
እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችውን እውቅና ተከትሎ ያደረገቻቸው ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶች በአፍሪካ ቀንድ የተፅዕኖ አድማሷን ለማስፋት እና በቀጠናው ወታደራዊ ቁመና እንዲኖራት ያስቻለ መሆኑን የቀጠናው ተንታኞች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይደመጣል።


