መጋቢት 8 2018 ዓ.ም–ብል ፖስት ዜና!
ከየመን የባሕር ዳርቻ ተነስተው ወደ ጂቡቲ ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይጓዙበት የነበረው ጀልባ ተገልብጦ መሞታቸውን በአደጋው ሰለባ የሆኑትን ቤተሰቦች እና የቅርብ ሰዎችን ዋቢ አድርጎ ተቀማጭነቱ በካናዳ የሆነው ሆርን ፍሪኩዌንሲ የተሰኘው የበይነ-መረብ ሚዲያ ዘግቧል።
በጀልባ መገልበጥ አደጋው ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ነዋሪነታቸውን በሳዑዲ አረቢያ ያደረጉ እንደነበሩ የገለፀው ሆርን ፍሪኩዌንሲ፣ በባሕር አቋርጠው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ቀይ ባሕር ላይ ባጋጠማቸው የጀልባ አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ዘግቧሎ።
የመገልበጥ አደጋ ያጋጠማት ጀልባ ኢትዮጵያንን ጨምሮ በግምት 150 ይሆናሉ የተባሉ የአፍሪካ ስደተኞችን ጭና ስትጓዝ እያለ በአደገኛ የባሕር ሞገድ ተመታ መገልበጧ ታውቋል።
በየመን ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በደረሰው የጀልባ መገልበጥ ቢያንስ 10 ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ተገልጿል። በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት ኢትዮጵያውያን መካከል የቅርብ ጓደኛዋ እንደሚገኝበት ሆርን ፍሪኩዌንሲ ነዋሪነቷን ሳዑዲ አረቢያ ካደረገች ወጣት አነጋግሮ ዘግቧል።
ወጣቷ እንደምትለው፣ በባሕር ሲጓዝ የሞተው ጓደኛዋ በሕገወጥ መንገድ ሳዑዲ አረቢያ ይኖር የነበረ ወጣት ሲሆን በባሕር ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሰ የነበረውም ሳውዲ አረቢያ በሕጋዊ መንገድ መኖር የሚችልበትን ሂደት ለማስፈጸም እንደነበር ጠቁማለች።
ወጣቷ “የልቤ ሰው መካሪዬ ወረቀት ላውጣ ብሎ በባሕር ሄደ፣ ሆዴ እየፈራ በሰላም ተመልስ ብዬው፣ ይሄው ባሕር በላው” በማለት እንባ እየተናነቃት ሁኔታውን አስረድታለች።
በደረሰው የጀልባ መገልበጥ አደጋ የተሳፈሩት ከሟቾቹ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያን መሆናቸውን ከባሕር ጠረፍ አዘዋዋሪዎች መስማቷን የገለፀችው ወጣቷ፣ የቅርብ ጎደኛዋን ጨምሮ ከ10 ያላነሱ ኢትዮጵያን ስደተኞች መሞታቸውን አዘዋዋሪዎቹ ነግረዋታል።
አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በባሕር ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱት በሕገወጥ መንገድ ከተሰደዱ በኋላ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ለማግኘት ነው ተብሏል። በርካታ ኢትዮጵያ በሳዑዲ ራሳቸውን ደብቀው በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ ቢሆንም፣ በነጻነት የሚፈልጉትን ሥራ ለመሥራት የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።ለዚህ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በሕጋዊ መንገድ ወረቀት አውጥተው ዳግም ወደ ሳዑዲ ለመመለስ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህም በህይወታቸው ተወራርደው መጀመሪያ በባሕር ወደ ኢትዮጵያ መመለስን ምርጫቸው ያደርጋሉ ሲል ሆርን ፍሪኩዌንሲ ዘግቧል።


