Friday, May 8, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችቢቢሲ አማርኛ በልዩ ዘገባው ያስነበበው የዐቢይ አህመድ መንግሥት በአማራ ህዝብ ላይ የከፈተው...

ቢቢሲ አማርኛ በልዩ ዘገባው ያስነበበው የዐቢይ አህመድ መንግሥት በአማራ ህዝብ ላይ የከፈተው ጦርነት፤ የደረሰዉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ እና ሰብዓዊ ቀውስ።

ሁለት አመታትን ባስቆጠረው የአቢይ አህመድ የብልፅግና መንግስት አገዛዝ በአማራ ህዝብ ላይ ባወጀው መጠነ ሰፊ ጦርነት ምክንያት የአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ እና ከፍተኛ ሰቆቃ እየደረሰበት እንደሆነ ቢቢሲ አማርኛ በሰራው ሰፊ ዘገባ ተገለፀ።

ቢቢሲ አማርኛ በሚያዝያ 6፣ 2017 ዓ.ም “ከቁጥር ባሻገር፤ ነዋሪውን ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ያለው የሁለት ዓመቱ የአማራ ክልል ግጭት” በሚል ርዕስ ባወጣው ልዩ ዘገባ እንደተመላከተው፣ የአማራ ክልል ከግንቦት 28፣ 2016 ዓ.ም አንስቶ ባልተራዘመ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (De facto State of Emergency) ስር እንደሚገኝ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ፣ የትምህርት እና የህክምና አገልግሎቶችን ጨምሮ የማህበራዊ ህይወት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መስተጓጎሉን በስፋት አትቷል።

በቢቢሲ አማርኛ ልዩ ዘገባ ከተካተቱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፣ ከሐምሌ 2015 እስከ መስከረም 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአምስት ሺህ ሴቶች በላይ የአስገድዶ መድፈር ሰለባ መሆናቸው አንዱ ነው። የአስገድዶ መድፈር ጥቃቱ አሃዝ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችልም ልዩ ዘገባው ጠቅሷል።

ዘገባው አያይዞ፤ አገዛዙ በአማራ ህዝብ ላይ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ፣ የቱሪዝም እና ተያያዥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መቀዛቀዙን ገልጿል። በቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ገቢ ከሚያስገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዷ የሆነችው ጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ጉዳቱ ካየለባቸው የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መካከል አንዷ ናት ሲል ቢቢሲ ያስረዳል።

በሆቴልና እና ቱሪዝም እንዲሁም በአስጎብኚነት የስራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ ዜጎች፣ ጦርነቱ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት “ስራ እስከማቆም መድረሳቸውን እና ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለመመገብ መቸገራቸውን” ጭምር ለቢቢሲ አማርኛ በምሬት አስረድተዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የከተማዋ ዋነኛ መለያ የሆኑት ጥንታዊ ውቅር አብያተክርስቲያናት “በከባድ መሳሪያ ንዝረት እና ፍንጣሪ” ስጋት እንዳደረባቸው የሐይማኖት አባቶች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ልዩ ዘገባው ሰብዓዊ ጉዳትን በተመለከተ የተለያዩ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን፣ በህዳር 25/2017 ዓ.ም በሸዋ ሮቢት ከተማ በመንግሥት ወታደሮች እና በፋኖ መካከል የነበረውን የተኩስ ልውውጥ በማውሳት፣ በአንድ ቤተሰብ ቤት ውስጥ የከባድ መሳሪያ ጥቃት በመንግሥት ወታደሮች አማካኝነት መፈፀሙን ተከትሎ የአራት ወር አራስ ህፃን በእናቷ እቅፍ ውስጥ እንዳለች መገደሏን ጠቅሷል። የቢቢሲ አማርኛ ልዩ ዘገባ እንደሚያትተው፣ በአማራ ክልል የጤና መዋቅር 100 የመንግሥት ሆስፒታሎች፣ 923 ጤና ጣቢያዎች፣ 3,725 ጤና ኬላዎች፣ 882 አምቡላንሶች እና ከ1,500 በላይ የግል የጤና ተቋማት እንደሚገኙ ጠቅሶ፣ እነዚህ የጤና ተቋማት እና የጤና ባለሙያዎች የድሮን ጥቃት ዒላማ መሆናቸውን ያስረዳል። የጤና ባለሙያዎች “ለፋኖ የህክምና እርዳታ ታደርጋላችሁ” በሚል በመንግሥት ወታደሮች ግድያን ጨምሮ የተለያዩ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸውም ጠቅሷል። 

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች