Wednesday, April 29, 2026

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችየመተከል ዞን ክልል ሆኖ እንዲዋቀር ለምክክር ኮሚሽኑ በአጀንዳነት ቀረበ፡፡

የመተከል ዞን ክልል ሆኖ እንዲዋቀር ለምክክር ኮሚሽኑ በአጀንዳነት ቀረበ፡፡

ከ1983 ዓመተ-ምህረት ወዲህ ከጎጃም ክፍለ ሀገር ተወስዶ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ የተካለለው የመተከል ዞን ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡

የመተከል ዞን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጥቶ ራሱን የቻለ ክልል ሆኖ እንዲዋቀር፣ በፓርቲያቸው በኩል ለኮሚሽኑ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ያደረጉት፣ የቦሮ ሺናሻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ናቸው።

ዶክተር መብራቱ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ “ዞኑ ቀደም ባሉት የአስተዳደር ዘመናት በጎጃም ክፍለ ሀገር ውስጥ የሚገኝ መሬት መሆኑን ተከትሎ አካባቢው የእኛ ነው የሚሉ አንዳንድ ኃይሎች ቢኖሩም፣ አካባቢው መሬት እንጂ ብሔር ባለመሆኑ የእኔ ርስት ነው የሚል ጥያቄ ሊቀርብበት አይገባም” ሲሉ አብራርተዋል።

ዶክተር መብራቱ አክለውም “መተከል ዞን በክልል ደረጃ ተዋቅሮ ሕዝቡ ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንደሚኖርበት የቦሮ ሺናሻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዉን አቅርቧል” ብለዋል፡፡

ከጎጃም ክፍለ ሀገር በኃይል ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተካለለው የመተከል መሬት፣ ልክ እንደ ወልቃይት እና ራያ “በጉልበት ወደሌሎች ክልሎች የተካለል የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ርስት ነው” በሚል ከፍተኛ ትግል እና መስዋዕትነት የተከፈለበት አካባቢ መሆኑ የሚታወስ ነው።

የዐቢይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣበት 2010 ዓመተ-ምህረት ወዲህ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በመንግሥት ታጣቂዎች፣ በኦነግ፣ እንዲሁም በጉሙዝ ታጣቂዎች አስከፊ በሆነ መንገድ በማንነታቸው ተለይተው መገደላቸው እና መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።

በአማራ ህዝብ ጠንካራ የማንነት እና ርስት ጥያቄ የሚነሳበት የመተከል ዞን፣ ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆን በሌሎች ኃይሎች ለምክክር ኮሚሽኑ በአጀንዳነት መቅረቡን ተከትሎ፣ በአማራ የፖለቲካ ኃይሎች በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች