የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በመተከል ዞን የምተገኘዋን ቡለን ከተማን በወረራ መቆጣጠራቸው ተሰምቷል። ታጣቂዎቹ ከዛሬ ንጋት አንስቶ ወደ አካባቢው መግባታቸውን፣ የዞብል ፖስት የመረጃ ምንጮች ከስፍራው ያደረሱን መረጃ ያሳያል።
የኦነግ ታጣቂዎች ከቡለን ከተማ በተጨማሪ፣ ድባጤ ተብሎ የሚጠራውን አካባቢ ጭምር ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተሰምቷል።
ታጣቂዎቹ በእነዚህ አካባቢዎች ጥቃት ሲፈፅሙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም፣ ከሰሞኑ እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ግን አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት እንደሚመስል ምንጮቻችን አያይዘው ገልፀዋል።
“በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፣ ፀጥታውም ደፍርሷል፣ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት ኃይሎች በአካባቢው ላይ የሉም” ሲሉ የዞብል ፖስት ምንጮች ሁኔታውን በጭንቀት ገልፀዋል።
የኦነግ ታጣቂዎች ወረራ የፈፀሙበት የመተከል ዞን፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጥቶ ራሱን የቻለ ክልል ሆኖ እንዲዋቀር፣ የቦሮ ሺናሻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ ማስገባቱ የሚታወስ ነው።
ይሄንን አስመልክቶ፣ “የኦነግ ታጣቂዎች ቡለን ከተማን ጨምሮ የመተከል ዞንን የተለያዩ አካባቢዎች ለመቆጣጠር ወረራ እየፈፀሙ የሚገኙት፣ አካባቢውን ወደ ኦሮሚያ ክልል እንጠቀልላን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው” ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአካባቢው ፖለቲካዊ ጉዳዮች አስተያየታቸውን በመስጠት የሚታወቁ የፖለቲካ ተንታኝ ለዞብል ፖስት አስረድተዋል።


