Saturday, June 14, 2025

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeማሕደረ-ታሪክየሰኔ ፩ የአዲስ አበባው ጭፍጨፋ እና በትውልድ ላይ ያኖረው ጠባሳ!

የሰኔ ፩ የአዲስ አበባው ጭፍጨፋ እና በትውልድ ላይ ያኖረው ጠባሳ!

በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሕዝቧ ላይ ጠባሳን አኑረው ያለፉ የተለያዩ ታሪካዊ ጥቁር ክስተቶች፣ በየዓመቱ ቀናቶቹ እየታወሱ ይዘከራሉ። በየካቲት 12 1928 ዓ.ም በፋሽስት ጣሊያን በአዲስአበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተፈፀመው አሳዛኝ ጭፍጨፋ፣ በህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም በተለምዶ 60ዎቹ ተብለው በሚጠሩት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ባለስልጣናት ላይ የተፈፀመው የግፍ ግድያ፣ ለአብነት ያህል በየዓመቱ የሚታሰቡ አሳዛኝ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው።

ልክ እንደነዚህ አሳዛኝ የታሪክ ስብራቶች ሁሉ፣ በሰኔ ፩፣ 1997 ዓ.ም፣ ምርጫ 97ን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ መንግሥት የተፈፀመው አሳዛኝ ጭፍጨፋ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በየዓመቱ እየታወሰ መዘከር ከጀመረ እነሆ ሃያ ዓመታት ተቆጠሩ።

ጊዜው 1997 ዓ.ም ነበር፡፡  ወቅቱ ኢትዮጵያ ተጠባቂውን አገራዊ ምርጫ ለማድረግ ሽር ጉድ እያለች የነበረበት ዘመን። ይህ ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውይይቶች የተፋፋሙበት፣ እንደ መስቀል አደባባይ ባሉ ታሪካዊ የህዝብ መሰባሰቢያ ስፍራዎች ታላላቅ የሕዝብ ሰልፎች እና ትይንቶች የተካሄዱበት፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የተሰባሰቡ በርካታ ታዛቢዎች የሚካሄደውን ምርጫ በንቃት ለመታዘብ በመላ አገሪቱ የተሰማሩበት ነበር።

በወቅቱ ከ26 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በመራጭነት የተመዘገቡበት፣ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ ጉልህ ውጤት ለማምጣት ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ (ቅንጅት) እንዲሁም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ሕብረት) የሚሉ ሁለት ጥምረቶችን ፈጥረው፣ ኢህአዴግን ለማሸነፍ በጠንካራ መንፈስ የተሰለፉበት ነበር።

በግንቦ 7/ 1997 ዓ.ም ሊደረግ ቀን በተቆረጠለት አገራዊ ምርጫ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለንተናዊ ለውጥን አመጣለሁ በሚል፣ ይወክሉኛል ላላቸው የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለሰዓታት ተሰልፎ ድምፁን ሰጠ።

በድምፅ ቆጠራው ወቅት የተቃዋሚ ኃይሎች አብላጫ ድምፅ የማግኘታቸው እድል ከፍተኛ እንደሆነ መነገር ጀመረ። ይሄንን ተከትሎ ስልጣኔን አሳልፌ አልሰጥም ያለው ኢህአዴግ፣ የምርጫውን ውጤት ለመጠምዘዝ እና የህዝብን ውሳኔ ለመቀልበስ ግልፅ እንቅስቃሴ ውስጥ ገባ።

የግንቦት 1997ቱ የምርጫ ሂደት እና በኢትዮጵያ ህዝብ የተፈጠረው ህዝባዊ መነቃቃትና የለውጥ ፍላጎት ያስፈራቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ “በኢትዮጵያ ሰልፍ እና ከቤት ውጭ የሚደረግ ህዝባዊ ስብሰባ ለአንድ ወር ያህል የተከለከለ ነው!” በማለት በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው አስጠነቀቁ። ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለው፣ “ውሳኔውን ተላልፈው በሚገኙ ወገኖች ላይ፣ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ጥብቅ እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ተላልፏል” አሉ።   

የተካሄደው ምርጫና የህዝብን የምርጫ ውሳኔ ለመቀልበስ የተደረገውን መንግሥታዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ የአዲስ አበባ ህዝብ “ድምፃችን ይከበር” በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ወጣ። አቶ መለስ ዜናዊ “የአደባባይ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን በሚያደርጉ ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰድ” ማለታቸውን ተከትሎ፣ የመንግስት ታጣቂዎች በአዲስ አበባ ለሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ንፁሃን ላይ አሰቃቂ በሆነ መልኩ የአውቶማቲክ ጥይት አዘነቡ።

ይህ አሳዛኝ ክስተት የተፈፀመው ልክ ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት ነበር። በዕለተ ረቡዕ ሰኔ ፩ ቀን፣ 1997 ዓ.ም በአቶ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ለመበተን የመንግሥት ታጣቂዎች የወሰዱት የኃይል እርምጃ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታይቶ የነበረውን የዲሞክራሲ የተስፋ ጭላንጭል በደም ያጨቀየ አሳዛኝ የታሪክ እጥፋት ሆነ።

ግድያውን ተከትሎ መንግስት ባወጣው ሪፖርት በቀኑ የተገደሉት 42 ናቸው ቢልም፣ በወቅቱ በከተማዋ የነበረውን ሀዘን በቅርበት የተከታተሉ ገለልተኛ ወገኖች ግን የሟቾች ቁጥር መንግሥት ካወጣው ሪፖርት በላይ እንደሆነ ገልፀዋል። በዚህም ከ200 በላይ የሚሆኑ ንፁሃን እንደተገደሉ እና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ተዘግቧል።

“የምርጫ ድምፃችን ይከበር” የሚል ሰላማዊ ሰልፍ ላይ  ተሳትፈው ከተገደሉት ንፁሃን አዲስ አበቤዎች መካከል፣ ታዳጊዎች፣ መንትያ ወንድማማቾች፣ አዛውንቶች፣ እንዲሁም እናቶች እንደሚገኙበት፣ በወቅቱ ክስተቱን የተመለከቱ የአይን እማኞች እና የግድያ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችን ዋቢ አድርገው በርካታ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ክስተቱ የመላውን ዓለም ትኩረት የሳበ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ በወቅቱ ተመድን በዋና ፀሐፊነት ይመሩ በነበሩበት ኮፊ አናን በኩል በይፋ አውግዟል።

ምርጫ 97 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ፣ ከፍተኛ ህዝባዊ መነቃቃትን የፈጠረ እና የለውጥ ፈላጊዎች ዘመንም ነበር። ይህ ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ፣ እንደ አንድ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ተደርጎ እንደሚወሰድ በርካታ ልሂቃን የሚስማሙበት ነው። አጋጣሚው በዚህ መልኩ ባይደናቀፍ ኖሮ፣ ምናልባትም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አስተማማኝ የዲሞክራሲ ባህልን የመገንባት ምዕራፍን የሚከፍት ዕድል ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያን እግር ከወርች ይዞ ወደፊት አላራምድ ያለውና ለዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የዳረጋት የዘር ፖለቲካ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ተካሂዶበት ማብቂያው ሊሆን የሚችልበት ዕድል ነበር ተብሎ ይገመታል።

ምርጫ 97 የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ተስፋ እና ህይወት ከቀጠፈ ወዲህ፣ በኢትዮጵያ ተደረጉ የተባሉት ሁሉም ምርጫዎች የይስሙላ ናቸው። መንግሥት በወቅቱ የተፈጠረውን ህዝባዊ መነቃቃት ለማኮላሸት እና ስልጣኑን በኃይል ለማስቀጠል ብዙ ስልቶችን ተግባራዊ አድርጓል።

የፖለቲካ ንቃት እና ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች በአሸባሪነት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ብሎ በመፈረጅ፣ ህገመንግስቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በማለት፣ በርካቶችን ለዓመታት በእስር ቤት እንዲማቅቁ ወይም ከሀገር እንዲሰደዱ አድርጓል። ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት የሌለባት ሀገር እንድትሆን ተደርጓል።      

ያ ጊዜ የብሩህ ተስፋ ጊዜ ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ ፖለቲካዊ ንቃትና ተሳትፎው ከፍ ያለበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር። ወቅቱ በትውልድ ላይ ያሳደረው ጠባሳ ቀላል የሚባል አይደለም። ክስተቱን ተከትሎ በርካታ የአዲስአበባ ወጣቶች ሀገራቸውን ጥለው በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተሰድደዋል። መንግሥትም የአዲስአበባ ነዋሪዎችን ማህበራዊ ግንኙነት በጥርጣሬ ከመመልከት አልፎ፣ ማህበረሰቡን ለመነጣጠል እና መተማመንን ለመሸርሸር በርካታ ስራዎችን ሰርቷል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የተደረጉ ፖለቲካዊ ንቅናቄዎች ያን ያህል ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም። ዛሬ የምንዘክረውን የምርጫ 97 ማግስት ጭፍጨፋ የፈፀመው ህወሓት ከስልጣን ቢወገድም፣ እሱን ተክቶ ወደ ስልጣን የመጣው የብልፅግናው አገዛዝም ጭቆናን፣ ፀረ-ህዝብነትን፣ ደም ማፍሰስን፣ ከትናንት በከፋ ሁኔታ አስቀጥሎት ይገኛል።

ዞብል ፖስት በሰኔ ፩ 1997 ዓ.ም ምርጫ ማግስት በግፈኛው የህወሓት አገዛዝ በአዲስ አበባ ከተማ በአሰቃቂ ሁኔታ ለተጨጨፈ ሰማዕታት፣ መታሰቢያ እንዲቆምላቸው ጥሪውን ያቀርባል።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች