Monday, June 16, 2025

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮች"ሐይማኖትን እና ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመ ነው" እናት ፓርቲ።

“ሐይማኖትን እና ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመ ነው” እናት ፓርቲ።

ሰኔ 2/2017 ዓ.ም- ዞብል ፖስት ዜና

ኦናት ፓርቲ “የካህኑና ምእመናኑ ግድያ የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ፕሮጀክቱ አካል ነው” በሚል በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

እናት ፓርቲ በዛሬው ዕለት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ፣ በግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ፣ የአንጎዴቼ ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በአገልጋዮች እና ምእመናኑ ላይ የተፈፀመውን ግድያ የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ፕሮጀክት አካል ነው በማለት አውግዟል።       

ፓርቲው በመግለጫው፣ “በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ፣ የአንጎዴቼ ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መምሬ ተስፉ ዓለሙ፣ የአጥቢያው አባትና ሀገር ሽማግሌ አቶ ክፍሌ ገብረ ክርስቶስ እና አቶ በጋሻው ሥዩምን በነዋሪዎች አጠራር “ሸኔ” በሚባለው ኃይል ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ 12:00 ላይ አስፓልት መንገድ ላይ አውጥተው ገድለዋቸዋል” በማለት ገልጿል። 

ፓርቲው አክሎም፣ “2 ሰዎች በጥይት ተመትተው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ እና ሌሎች 5 ሰዎች ታፍነው ተወስደው የደረሱበት አልታወቀም” በማለት በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

እናት ፓርቲ፣ በአካባቢው ተደጋጋሚ ሐይማኖትና ማንነትን ማዕከል ያደረገ ጭፍጨፋ እንደሚፈፀም ጠቅሶ፣ “በግንቦት 10 ቀን መሪጌታ ቀለመወርቅ የተባሉን የሐይማኖት አባት ለመግደል ፈልገው ሲያጡ፣ የአራት ልጆች እናት የሆኑትን ባለቤታቸውን በሌሊት ገድለዋቸው ሄደዋል” በማለት ገልጿል።

ፓርቲው አያይዞ፣ “በዞኑ ሽርካ ወረዳ ካለፈው ዓመት 2016 ዓ.ም መስከረም ጀምሮ ካህናትን ጨምሮ 113 ንጹሓን በግፍ ተጨፍጭፈዋል፤ ከ30 በላይ ታፍነው ተወስደው የደረሱበት አልታወቀም” ብሏል፡፡ በተጨማሪም፣ በርካታ ንብረት መውደሙን እና ከ80 ጥማድ በላይ የእርሻ ከብቶች መዘረፋቸውን አሳውቋ፡፡

እናት ፓርቲ የአካባቢውን ነዋሪዎች ማነጋገሩን በመግለፅ፣ በተጠቀሱት አካባቢዎች “ሐይማኖትን ለይተው ጭፍጨፋው እንደሚፈፅሙባቸው እና አካባቢያቸው ሞት ያንዣበበት ነው” በማለት ያነጋገራቸውን ነዋሪዎች ሥጋት በመግለጫው አካትቷል።

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የእልቂት ምድር መሆኑን ጠቅሶ፣ “ሁኔታው የመንግሥትም የሚዲያም ትኩረት ሊያገኝ ባለመቻሉ በአካባቢው በነጋ ቁጥር አዳዲስ እልቂት እተፈፀመ ቀጥሏል” ሲል እናት ፓርቲ በመግለጫው ያስረዳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የክልሉ ባለስልጣናት ግድያውን ከሚፈፅሙ ታጣቂ ኃይሎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ በመግለጫው ተመላክቷል።

እናት ፓርቲ “በአካባቢው የሚፈጸመው ጭፍጨፋ ሐይማኖትንና ማንነትን ማዕከል ያደረገ የተቀናጀ ዘር ጭፍጨፋ” ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጾ፣ እየተፈፀመ ያለው ወንጀል ዓለምአቀፍ የሕግ ተጠያቂነትን ማምጣቱ እንደማይቀር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስረድቷል፡፡

ፓርቲው ለሞቱት ወገኖች ልባዊ ሐዘኑን በመግለፅ እና ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን በመመኘት፣ “ታፍነው የተወሰዱ ንጹሓን ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እንዲፈቱ እንጠይቃለን!” በማለት መግለጫውን ለህዝብ ይፋ አድርጓል። 

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች