Tuesday, June 24, 2025

INFORMING WITH FIDELITY

ለማስታወቂያ ክፍት ነው

Homeሀገራዊ ጉዳዮችበዝቋላ ገዳም በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በመነኮሳት ላይ ግድያ ተፈፀመ።

በዝቋላ ገዳም በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በመነኮሳት ላይ ግድያ ተፈፀመ።

ሰኔ 16/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!

በታሪካዊው ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ  ቅዱስ ገዳም የሚኖሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የገዳሙ መነኮሳት በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በትናንትናው ዕለት ተገድለዋል።

ከተገደሉት በተጨማሪ ታፍነው የተወሰዱ መነኮሳት መኖራቸው የተነገረ ሲሆን፣ ድርጊቱ የተፈፀመው በኦነግ ታጣቂዎች እንደሆነ ሁኔታውን አስመልክቶ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኦነግ ታጣቂዎች በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ  ቅዱስ ገዳም በሚኖሩ መነኮሳት ላይ ግድያ እና አፈና ሲፈፅሙ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኘው ታሪካዊው ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ውስጥ የሚኖሩ መነኮሳት፣ በሰኔ 15/2017 ዓ.ም በታጣቂ ኃይሎች መገደላቸውን የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት በትናንትናው ዕለት ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

በዚህ ጥቃት ከተገደሉት መነኮሳት በተጨማሪ፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሌሎች መነኮሳትም ታፍነው መወሰዳቸውን የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ አገልግሎት የገዳሙን አባቶች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ሰኔ 15/ 2017 ዓ.ም በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ  ቅዱስ ገዳም ላይ የተፈፀመው ጥቃት በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደገመ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በየካቲት 2016 ዓ.ም ላይም በተመሳሳይ መልኩ አራት መነኮሳት በኦነግ ታጣቂዎች መገደላቸውና ሌሎች የገዳሙ አባቶች ታፍነው መወሰዳቸው የሚታወስ ነው።

ይህ ተደጋጋሚ ጥቃት በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች እና አማኞች ላይ የሚፈፀመው መጠነ ሰፊ ጥቃት አንዱ አካል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል በጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ አፅንኦት ሰጥተው አስተያየታቸውን የሚያጋሩ በርካቶች ናቸው።

በክልሉ መሰል ጥቃቶች በየጊዜው የሚፈፀሙ ሲሆን፣ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ በቤተክርስቲያኗ ላይ ለሚፈፀሙ ጥቃቶች ተባባሪ እንደሆኑ በየጊዜው የሚቀርቡ ወቀሳዎች ያመላክታሉ።   

ከዚህ ቀደም በተፈጸመው ጥቃት የመከላከያ ሠራዊቱ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በገዳሙ የተፈፀመውን ግድያ ማስተባበላቸው የሚታወስ ነው። ይህ የመንግስት አካላት ምላሽ እና የጥቃቱ ተደጋጋሚነት በገዳሙ አካባቢ የጸጥታውን ሁኔታ የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል።

የዚህ የቅርብ ጊዜ ጥቃት ፈጻሚዎች የኦነግ ታጣቂዎች እንደሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ሁኔታ በአካባቢው ያለውን አሳሳቢ የሠላም ሁኔታ እና በሃይማኖት ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለውን የማያባራ በደል አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ  ቅዱስ ገዳም ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ የገዳሙ አባቶች መገደላቸውን እና ታፍነው መወሰዳቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ቢሆንም፣ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።

RELATED ARTICLES

በጣም የተወደዱ

የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች